1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 11:1-32

Ethiopian Amharic Bible (AMH)

1እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እኔን ምሰሉ።

2ወንድሞች ሆይ፥ በሁሉ ስለምታስቡኝና አሳልፌ እንደ ሰጠኋችሁ ወግን ፈጽማችሁ ስለ ያዛችሁ አመሰግናችኋለሁ።

3ነገር ግን የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ፥ የሴትም ራስ ወንድ፥ የክርስቶስም ራስ እግዚአብሔር እንደ ሆነ ልታውቁ እወዳለሁ።

4ራሱን ተከናንቦ የሚጸልይ ወይም ትንቢት የሚናገር ወንድ ሁሉ ራሱን ያዋርዳል።

5ራስዋን ሳትሸፍን ግን የምትጸልይ ወይም ትንቢት የምትናገር ሴት ሁሉ ራስዋን ታዋርዳለች፤ እንደ ተላጨች ያህል አንድ ነውና።

6ሴትም ራስዋን ባትሸፍን ጠጉርዋን ደግሞ ትቆረጥ፤ ለሴት ግን ጠጉርዋን መቆረጥ ወይም መላጨት የሚያሳፍር ከሆነ ራስዋን ትሸፍን።

7ወንድ የእግዚአብሔር ምሳሌና ክብር ስለ ሆነ ራሱን መከናነብ አይገባውም፤ ሴት ግን የወንድ ክብር ናት።

8ሴት ከወንድ ናት እንጂ ወንድ ከሴት አይደለምና።

9ሴት ስለ ወንድ ተፈጠረች እንጂ ወንድ ስለ ሴት አልተፈጠረምና።

10ስለዚህ ሴት ከመላእክት የተነሣ በራስዋ ሥልጣን ሊኖራት ይገባል።

11ነገር ግን በጌታ ዘንድ ሴት ያለ ወንድ ወንድም ያለ ሴት አይሆንም።

12ሴት ከወንድ እንደ ሆነች እንዲሁ ወንድ ደግሞ በሴት ነውና፤ ሁሉም ከእግዚአብሔር ነው።

13በእናንተ በራሳችሁ መካከል ፍረዱ፤ ሴት ራስዋን ሳትሸፍን ወደ እግዚአብሔር ልትጸልይ ይገባታልን?

15ዳሩ ግን ማንም ሊከራከር ቢፈቅድ፥ እኛ ወይም የእግዚአብሔር አብያተ ክርስቲያናት እንዲህ ያለ ልማድ የለንም።

16ነገር ግን በምትሰበሰቡበት ጊዜ ለሚከፋ እንጂ ለሚሻል ስላልሆነ ይህን ትእዛዝ ስሰጥ የማመሰግናችሁ አይደለም።

17በመጀመሪያ ወደ ማኅበር ስትሰበሰቡ በመካከላችሁ መለያየት እንዳለ እሰማለሁና፥ በአንድ በኩልም አምናለሁ።

18በእናንተ ዘንድ የተፈተኑት እንዲገለጡ በመካከላችሁ ወገኖች ደግሞ ሊሆኑ ግድ ነውና።

19እንግዲህ አብራችሁ ስትሰበሰቡ የምትበሉት የጌታ እራት አይደለም፤

20በመብላት ጊዜ እያንዳንዱ የራሱን እራት ይበላልና፥ አንዱም ይራባል አንዱ ግን ይሰክራል።

21የምትበሉባቸውና የምትጠጡባቸው ቤቶች የላችሁምን? ወይስ የእግዚአብሔርን ማኅበር ትንቃላችሁን አንዳችም የሌላቸውን ታሳፍራላችሁን? ምን ልበላችሁ? በዚህ ነገር ላመስግናችሁን? አላመሰግናችሁም።

22ለእናንተ ደግሞ አሳልፌ የሰጠሁትን እኔ ከጌታ ተቀብያለሁና፤

23ጌታ ኢየሱስ አልፎ በተሰጠበት በዚያች ሌሊት እንጀራን አንሥቶ አመሰገነ፥ ቆርሶም። እንካችሁ ብሉ፤ ይህ ስለ እናንተ የሚሆን ሥጋዬ ነው፤ ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት አለ።

24እንደዚሁም ከእራት በኋላ ጽዋውን ደግሞ አንሥቶ። ይህ ጽዋ በደሜ የሚሆን አዲስ ኪዳን ነው፤ በጠጣችሁት ጊዜ ሁሉ ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት አለ።

25ይህን እንጀራ በበላችሁ ጊዜ ሁሉ፥ ይህንም ጽዋ በጠጣችሁ ጊዜ ሁሉ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ሞቱን ትናገራላችሁና።

26ስለዚህ ሳይገባው ይህን እንጀራ የበላ ወይም የጌታን ጽዋ የጠጣ ሁሉ የጌታ ሥጋና ደም ዕዳ አለበት።

27ሰው ግን ራሱን ይፈትን፥ እንዲሁም ከእንጀራው ይብላ ከጽዋውም ይጠጣ፤

28ሳይገባው የሚበላና የሚጠጣ የጌታን ሥጋ ስለማይለይ ለራሱ ፍርድ ይበላልና፥ ይጠጣልምና።

29ስለዚህ በእናንተ ዘንድ የደከሙና የታመሙ ብዙዎች አሉ አያሌዎችም አንቀላፍተዋል።

30ራሳችንን ብንመረምር ግን ባልተፈረደብንም ነበር፤

31ነገር ግን በተፈረደብን ጊዜ ከዓለም ጋር እንዳንኮነን በጌታ እንገሠጻለን።

32ስለዚህ፥ ወንድሞቼ ሆይ፥ ለመብላት በተሰበሰባችሁ ጊዜ እርስ በርሳችሁ ተጠባበቁ።

33ማንም የራበው ቢኖር ለፍርድ እንዳትሰበሰቡ በቤቱ ይብላ። የቀረውንም ነገር በመጣሁ ጊዜ እደነግጋለሁ።