መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ። 11:1-39
Ethiopian Amharic Bible (AMH)
1ንጉሡም ሰሎሞን ከፈርዖን ልጅ ሌላ፥ በሞዓባውያንና በአሞናውያን በኤዶማውያን በሲዶናውያንና በኬጢያውያን ሴቶች፥ በብዙ እንግዶች ሴቶች ፍቅር ተነደፈ።
2እግዚአብሔር የእስራኤልን ልጆች። አምላኮቻቸውን ትከተሉ ዘንድ ልባችሁን በእውነት ያዘነብላሉና ወደ እነርሱ አትግቡ፥ እነርሱም ወደ እናንተ አይግቡ ካላቸው ከአሕዛብ፥ ከእነዚህ ጋር ሰሎሞን በፍቅር ተጣበቀ።
3ለእርሱም ወይዛዝር የሆኑ ሰባት መቶ ሚስቶች ሦስት መቶም ቁባቶች ነበሩት፤ ሚስቶቹም ልቡን አዘነበሉት።
4ሰሎሞንም ሲሸመግል ሚስቶቹ ሌሎችን አማልክት ይከተል ዘንድ ልቡን አዘነበሉት፤ የአባቱ የዳዊት ልብ ከአምላኩ ከእግዚአብሔር ጋር ፍጹም እንደ ነበረ የሰሎሞን ልቡ እንዲሁ አልነበረም።
5ሰሎሞንም የሲዶናውያንን አምላክ አስታሮትን፥ የአሞናውያንንም ርኵሰት ሚልኮምን፥ ተከተለ።
6ሰሎሞንም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገርን አደረገ፥ እንደ አባቱም እንደ ዳዊት እግዚአብሔርን በመከተል ፍጹም አልሆነም።
7በዚያን ጊዜም ሰሎሞን ለሞዓብ ርኵሰት ለካሞሽ፥ ለአሞንም ልጆች ርኵሰት ለሞሎክ በኢየሩሳሌም ፊት ለፊት ባለው ተራራ ላይ መስገጃ ሠራ።
8ለአማልክቶቻቸው ዕጣን ለሚያጥኑ መሥዋዕትም ለሚሠዉ ለእንግዶች ሚስቶቹ ሁሉ እንዲሁ አደረገ።
10እግዚአብሔርም ሰሎሞንን አለው። ይህን ሠርተሃልና፥ ያዘዝሁህንም ቃል ኪዳኔንና ሥርዓቴን አልጠበቅህምና መንግሥትህን ከአንተ ቀዳድጄ ለባሪያህ እሰጠዋለሁ።
11ነገር ግን ከልጅህ እጅ እቀድደዋለሁ እንጂ ስለ አባትህ ስለ ዳዊት ይህን በዘመንህ አላደርግም።
12ነገር ግን ስለ ባሪያዬ ስለ ዳዊትና ስለ መረጥኋት ስለ ኢየሩሳሌም ለልጅህ አንድ ነገድ እሰጣለሁ እንጂ መንግሥቱን ሁሉ አልቀድድም።
13እግዚአብሔርም ከኤዶምያስ ነገሥታት ዘር የኤዶምያስን ሰው ሃዳድን ጠላት አድርጎ በሰሎሞን ላይ አስነሣው።
15ሃዳድ ገና ብላቴና ሳለ ሃዳድና ከእርሱ ጋር ጥቂቶቹ ከኤዶምያስ ሰዎች የሆኑ የአባቱ ባሪያዎች ወደ ግብጽ ኰብልለው ነበር።
16ከምድያምም ተነሥተው ወደ ፋራን መጡ፤ ከእነርሱም ጋር ከፋራን ሰዎች ወሰዱ፥ ወደ ግብጽም መጡ፥ ወደ ግብጽም ንጉሥ ወደ ፈርዖን ዘንድ ገቡ፤ እርሱም ቤት ሰጥቶ ቀለብ ዳረገው፥ ምድርም ሰጠው።
17የሚስቱንም የእቴጌይቱን የቴቄምናስን እኅት እስኪያጋባው ድረስ ሃዳድ በፈርዖን ፊት እጅግ ባለምዋል ሆነ።
18የቴቄምናስ እኅት ጌንባትን ወለደችለት፥ ቴቄምናስም በፈርዖን ቤት አሳደገችው፤ ጌንባትም በፈርዖን ቤት በፈርዖን ልጆች መካከል ነበረ።
19ሃዳድም በግብጽ ሳለ ዳዊት ከአባቶቹ ጋር እንዳንቀላፋ፥ የሠራዊቱም አለቃ ኢዮአብ እንደ ሞተ በሰማ ጊዜ፥ ሃዳድ ፈርዖንን። ወደ አገሬ እሄድ ዘንድ አሰናብተኝ አለው።
20ፈርዖንም። እነሆ፥ ከእኔ ዘንድ ወደ አገርህ መሄድ የፈለግህ ምን አጥተህ ነው? አለው። እርሱም። አንዳች አላጣሁም፤ ነገር ግን ልሂድ ብሎ መለሰ። ሃዳድም ወደ አገሩ ተመለሰ፥ ሃዳድም ያደረገው ክፉ ነገር ይህ ነው፤ እስራኤልን አስጨነቀ፥ በኤዶምያስም ላይ ነገሠ።
21እግዚአብሔርም ደግሞ ከጌታው ከሱባ ንጉሥ ከአድርአዛር የኰበለለውን የኤልያዳን ልጅ ሬዞንን ጠላት አድርጎ አስነሣበት።
22ዳዊትም የሱባን ሰዎች በገደለ ጊዜ ሬዞን ሰዎችን ሰብስቦ የጭፍራ አለቃ ሆነ፤ ወደ ደማስቆም ሄዱ፥ በዚያም ተቀመጡ፤ በደማስቆም ላይ አነገሡት።
23ሃዳድም ካደረገው ክፋት ሌላ በሰሎሞን ዘመን ሁሉ የእስራኤል ጠላት ነበረ።
24ከሳሪራ አገር የሆነ የሰሎሞን ባሪያ የኤፍሬማዊው የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም በንጉሡ ላይ ዐመፀ፤ እናቱም ጽሩዓ የተባለች ባልቴት ሴት ነበረች።
25በንጉሡም ያመፀበት ምክንያት ይህ ነው፤ ሰሎሞን ሚሎን ሠራ፥ የአባቱንም የዳዊትን ከተማ ሰባራውን ጠገነ።
26ኢዮርብዓምም ጽኑዕ ኃያል ሰው ነበረ፤ ሰሎሞንም ጕልማሳው በሥራ የተመሰገነ መሆኑን ባየ ጊዜ በዮሴፍ ነገድ ሥራ ሁሉ ላይ ሾመው።
27በዚያን ጊዜም ኢዮርብዓም ከኢየሩሳሌም በወጣ ጊዜ ሴሎናዊው ነቢዩ አኪያ በመንገድ ላይ ተገናኘው፤ አኪያም አዲስ ልብስ ለብሶ ነበር ሁለቱም በሜዳው ለብቻቸው ነበሩ።
28አኪያም የለበሰውን አዲስ ልብስ ይዞ ከአሥራ ሁለት ቈራረጠው።
29ኢዮርብዓምንም አለው። አሥር ቍራጭ ውሰድ፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። እነሆ፥ ከሰሎሞን እጅ መንግሥቱን እቀድዳለሁ፥ አሥሩንም ነገዶች እሰጥሃለሁ፤
30ስለ ባሪያዬ ስለ ዳዊት ከእስራኤልም ነገድ ስለ መረጥኋት ከተማ ስለ ኢየሩሳሌም ግን አንድ ነገድ ይቀርለታል፤
31ጥለውኛልና፥ ለሲዶናውያንም አምላክ ለአስታሮት፥ ለሞዓብም አምላክ ለካሞሽ፥ ለአሞንም ልጆች አምላክ ለሚልኮም ሰግደዋልና፥ አባቱም ዳዊት እንዳደረገ በፊቴ ቅን ነገር ያደርጉ ዘንድ፥ ሥርዓቴንና ፍርዴንም ይጠብቁ ዘንድ በመንገዴ አልሄዱምና።
32መንግሥቱንም ሁሉ ከእጁ አልወስድም፤ ትእዛዜንና ሥርዓቴን ስለ ጠበቀው ስለ መረጥሁት ስለ ባሪያዬ ስለ ዳዊት ግን በዕድሜው ሁሉ አለቃ አደርገዋለሁ።
33መንግሥቱንም ከልጁ እጅ እወስዳለሁ፥ ለአንተም አሥሩን ነገድ እሰጥሃለሁ።
34ስሜንም ባኖርሁባት በዚያች በመረጥኋት ከተማ በኢየሩሳሌም ለባሪያዬ ለዳዊት በፊቴ ሁልጊዜ መብራት ይሆንለት ዘንድ ለልጁ አንድ ነገድ እሰጠዋለሁ።
35አንተንም እወስድሃለሁ፥ ነፍስህም በወደደችው ሁሉ ላይ ትነግሣለች፥ በእስራኤልም ላይ ንጉሥ ትሆናለህ።
36ባሪያዬም ዳዊት እንዳደረገ፥ ያዘዝሁህን ሁሉ ብትሰማ፥ በመንገዴም ብትሄድ፥ በፊቴም የቀናውን ብታደርግ፥ ሥርዓቴንና ትእዛዜን ብትጠብቅ፥ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፥ ለዳዊትም እንደ ሠራሁለት ጽኑ ቤት እሠራልሃለሁ፥ እስራኤልንም ለአንተ እሰጥሃለሁ።
37ስለዚህም የዳዊትን ዘር አስጨንቃለሁ፤ ነገር ግን በዘመን ሁሉ አይደለም።
38ሰሎሞንም ኢዮርብዓምን ሊገድለው ወደደ፤ ኢዮርብዓምም ተነሥቶ ወደ ግብጽ ኰበለለ፥ ወደ ግብጽም ንጉሥ ወደ ሺሻቅ መጣ፥ ሰሎሞንም እስኪሞት ድረስ በግብጽ ተቀመጠ።
39የቀረውም የሰሎሞን ነገር፥ ያደረገውም ሁሉ፥ ጥበቡም፥ እነሆ፥ በሰሎሞን ታሪክ መጽሐፍ ተጽፎአል።
40ሰሎሞንም በኢየሩሳሌም በእስራኤል ሁሉ ላይ የነገሠበት ዘመን አርባ ዓመት ነበረ።
41ሰሎሞንም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በአባቱም በዳዊት ከተማ ተቀበረ፤ ልጁም ሮብዓም በፋንታው ነገሠ።