ትንቢተ አሞጽ 7:1-15
Ethiopian Amharic Bible (AMH)
1ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ አሳየኝ፤ እነሆም፥ የኋለኛው ሣር በሚበቅልበት መጀመሪያ ላይ አንበጣን ፈጠረ፤ እነሆም፥ ከንጉሡ አጨዳ በኋላ የበቀለ የገቦ ነበረ።
2የምድሩንም ሣር በልተው ከጨረሱ በኋላ፥ እኔ። ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ ይቅር እንድትል እለምንሃለሁ፤ ያዕቆብ ታናሽ ነውና እንዴት ይቆማል? አልሁ።
3እግዚአብሔርም ስለዚህ ነገር ተጸጸተ፤ ይህ አይሆንም፥ ይላል እግዚአብሔር።
4ጌታ እግዚአብሔርም እንዲህ አሳየኝ፤ እነሆም፥ ጌታ እግዚአብሔር በእሳት ለመፍረድ ጠራ፤ እርስዋም ታላቁን ቀላይና ምድርን በላች።
5እኔም። ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ እንድትተው እለምንሃለሁ፤ ያዕቆብ ታናሽ ነውና እንዴት ይቆማል? አልሁ።
6እግዚአብሔርም ስለዚህ ነገር ተጸጸተ፤ ይህ ደግሞ አይሆንም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
7እንዲህም አሳየኝ፤ እነሆም፥ ጌታ ቱንቢውን ይዞ በቱንቢ በተሠራ ቅጥር ላይ ቆሞ ነበር።
8እግዚአብሔርም። አሞጽ ሆይ፥ የምታየው ምንድር ነው? አለኝ። እኔም። ቱንቢ ነው አልሁ። ጌታም። እነሆ፥ በሕዝቤ በእስራኤል መካከል ቱንቢ አደርጋለሁ፤ ከእንግዲህም ወዲህ ደግሞ አላልፋቸውም፤
9የይስሐቅም የኮረብታው መስገጃዎች ይፈርሳሉ፥ የእስራኤልም መቅደሶች ባድማ ይሆናሉ፤ በኢዮርብዓምም ቤት ላይ በሰይፍ እነሣለሁ አለ።
11አሜስያስም አሞጽን። ባለ ራእዩ ሆይ፥ ሂድ ወደ ይሁዳም ምድር ሽሽ፥ በዚያም እንጀራን ብላ፥
12በዚያም ትንቢትን ተናገር፤ ነገር ግን ቤቴል የንጉሥ መቅደስና የመንግሥት ቤት ናትና ከእንግዲህ ወዲህ በዚህ ደግሞ ትንቢት አትናገር አለው።
13አሞጽም መልሶ አሜስያስን አለው። እኔ ላም ጠባቂና ወርካ ለቃሚ ነኝ እንጂ ነቢይ ወይም የነቢይ ልጅ አይደለሁም፤
14እግዚአብሔርም በጎቹን ከመከተል ወሰደኝ፥ እግዚአብሔርም። ሂድ፥ ለሕዝቤም ለእስራኤል ትንቢት ተናገር አለኝ።
15አሁንም የእግዚአብሔርን ቃል ስማ፤ አንተ። በእስራኤል ላይ ትንቢት አትናገር፥ በይስሐቅም ቤት ላይ አትስበክ ብለሃል፤
16ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ሚስትህ በከተማይቱ ውስጥ ጋለሞታ ትሆናለች፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆችህም በሰይፍ ይወድቃሉ፥ ምድርህም በገመድ ትከፈላለች፤ አንተም በረከሰች ምድር ትሞታለህ፥ እስራኤልም ከምድሩ ተማርኮ ይሄዳል።