ትንቢተ ዳንኤል 9:1-25
Ethiopian Amharic Bible (AMH)
1በከለዳውያን መንግሥት ላይ በነገሠ፥ ከሜዶን ዘር በነበረ በአሕሻዊሮስ ልጅ በዳርዮስ በመጀመሪያ ዓመት፥
2በነገሠ በመጀመሪያው ዓመት እኔ ዳንኤል የኢየሩሳሌም መፍረስ የሚፈጸምበትን ሰባውን ዓመት፥ እግዚአብሔር በቃሉ ለነቢዩ ለኤርምያስ የተናገረውን የዓመቱን ቍጥር በመጽሐፍ አስተዋልሁ።
3ማቅ ለብሼ በአመድም ላይ ሆኜ ስጾም እጸልይና እለምን ዘንድ ፊቴን ወደ ጌታ ወደ አምላክ አቀናሁ።
4ወደ አምላኬም ወደ እግዚአብሔር ጸለይሁ፥ ተናዝዤም እንዲህ አልሁ። ጌታ ሆይ፥ ከሚወድዱህና ትእዛዝህን ከሚፈጽሙ ጋር ቃል ኪዳንንና ምሕረትን የምትጠብቅ ታላቅና የምታስፈራ አምላክ ሆይ፥
5ኃጢአትን ሠርተናል፥ በድለንማል፥ ክፋትንም አድርገናል፥ ዐምፀንማል፥ ከትእዛዝህና ከፍርድህም ፈቀቅ ብለናል፤
6በስምህም ለነገሥታቶቻችንና ለአለቆቻችን ለአባቶቻችንም ለአገሩም ሕዝብ ሁሉ የተናገሩትን ባሪያዎችህን ነቢያትን አልሰማንም።
7ጌታ ሆይ፥ ጽድቅ ለአንተ ነው፤ እንደ ዛሬም ለእኛ ለይሁዳ ሰዎችና በኢየሩሳሌም ለሚቀመጡ ለእስራኤልም ሁሉ በቅርብና በሩቅም ላሉት አንተን በበደሉበት በበደላቸው ምክንያት በበተንህበት አገር ሁሉ የፊት እፍረት ነው።
8ጌታ ሆይ፥ በአንተ ላይ ኃጢአት ስለ ሠራን ለእኛና ለነገሥታቶቻችን ለአለቆቻችንና ለአባቶቻችንም የፊት እፍረት ነው።
10እስራኤልም ሁሉ ሕግህን ተላልፈዋል፥ ቃልህንም እንዳይሰሙ ፈቀቅ ብለዋል፤ በእርሱ ላይ ኃጢአት ሠርተናልና በእግዚአብሔር ባሪያ በሙሴ ሕግ የተጻፈው መሐላና እርግማን ፈሰሰብን።
11እጅግ ክፉ ነገርንም በእኛ ላይ በማምጣቱ በላያችንና በእኛ ዘንድ በተሾሙት ፈራጆቻችን ላይ የተናገረውን ቃል አጸና፤ በኢየሩሳሌምም ላይ እንደ ተደረገው ያለ ነገር ከቶ ከሰማይ ሁሉ በታች አልተደረገም።
12በሙሴም ሕግ እንደ ተጻፈ ይህ ክፉ ነገር ሁሉ መጣብን፤ ከኃጢአታችንም እንመለስ እውነትህንም እናስብ ዘንድ ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር ፊት አልለመንንም።
13ስለዚህም እግዚአብሔር ክፉ ነገሩን ጠብቆ በእኛ ላይ አመጣ፤ አምላካችን እግዚአብሔር በሚሠራው ሥራ ሁሉ ጻድቅ ነውና፥ እኛም ቃሉን አልሰማንምና።
14አሁንም ሕዝብህን ከግብጽ ምድር በበረታች እጅ ያወጣህ፥ እንደ ዛሬም ቀን ዝና ለአንተ ያገኘህ ጌታ አምላካችን ሆይ፥ ኃጢአትን ሠርተናል፥ ክፋትንም አድርገናል።
15ጌታ ሆይ፥ ስለ ኃጢአታችንና ስለ አባቶቻችን በደል ኢየሩሳሌምና ሕዝብህ በዙሪያችን ላሉት ሁሉ መሰደቢያ ሆነዋልና እንደ ጽድቅህ ሁሉ ቍጣህና መዓትህ ከከተማህ ከኢየሩሳሌም ከቅዱስ ተራራህ እንዲመለስ እለምንሃለሁ።
16አሁንም፥ አምላካችን ሆይ፥ የባሪያህን ጸሎትና ልመናውን ስማ፤ ጌታ ሆይ፥ በፈረሰው በመቅደስህ ላይ ስለ አንተ ስትል ፊትህን አብራ።
17አምላኬ ሆይ፥ በፊትህ የምንለምን ስለ ብዙ ምሕረትህ ነው እንጂ ስለ ጽድቃችን አይደለምና ጆሮህን አዘንብለህ ስማ፤ ዓይንህን ገልጠህ ጥፋታችንና ስምህ የተጠራባትን ከተማ ተመልከት።
18አቤቱ፥ ስማ፤ አቤቱ፥ ይቅር በል፤ አቤቱ፥ አድምጥና አድርግ፤ አምላኬ ሆይ፥ ስምህ በከተማህና በሕዝብህ ላይ ተጠርቶአልና ስለ ራስህ አትዘግይ።
19እኔም ገና ስናገር ስጸልይ፥ በኃጢአቴና በሕዝቤም በእስራኤል ኃጢአት ስናዘዝ፥ በአምላኬም በእግዚአብሔር ፊት ስለ ተቀደሰው ስለ አምላኬ ተራራ ስለምን፥
20ገናም በጸሎት ስናገር አስቀድሜ በራእይ አይቼው የነበረው ሰው ገብርኤል እነሆ እየበረረ መጣ፤ በማታም መሥዋዕት ጊዜ ዳሰሰኝ።
21አስተማረኝም፥ ተናገረኝም እንዲህም አለ። ዳንኤል ሆይ፥ ጥበብንና ማስተዋልን እሰጥህ ዘንድ አሁን መጥቻለሁ።
22አንተ እጅግ የተወደድህ ነህና በልመናህ መጀመሪያ ላይ ትእዛዝ ወጥቶአል፥ እኔም እነግርህ ዘንድ መጥቻለሁ፤ አሁንም ነገሩን መርምር፥ ራእዩንም አስተውል።
23ዓመፃን ይጨርስ፥ ኃጢአትንም ይፈጽም፥ በደልንም ያስተሰርይ፥ የዘላለምን ጽድቅ ያገባ፥ ራእይንና ትንቢትን ያትም፥ ቅዱሰ ቅዱሳኑንም ይቀባ ዘንድ በሕዝብህና በቅድስት ከተማህ ላይ ሰባ ሱባዔ ተቀጥሮአል።
24ስለዚህ እወቅ አስተውልም፤ ኢየሩሳሌምን መጠገንና መሥራት ትእዛዙ ከሚወጣበት ጀምሮ እስከ አለቃው እስከ መሢሕ ድረስ ሰባት ሱባዔና ስድሳ ሁለት ሱባዔ ይሆናል፤ እርስዋም በጭንቀት ዘመን ከጎዳናና ከቅጥር ጋር ትሠራለች።
25ከስድሳ ሁለት ጊዜ ሰባትም በኋላ መሢሕ ይገደላል፥ በእርሱም ዘንድ ምንም የለም፤ የሚመጣውም አለቃ ሕዝብ ከተማይቱንና መቅደሱን ያጠፋሉ፤ ፍጻሜውም በጐርፍ ይሆናል፥ እስከ መጨረሻም ድረስ ጦርነት ይሆናል፤ ጥፋትም ተቀጥሮአል።
26እርሱም ከብዙ ሰዎች ጋር ጽኑ ቃል ኪዳን ለአንድ ሱባዔ ያደርጋል፤ በሱባዔውም እኵሌታ መሥዋዕቱንና ቍርባኑን ያስቀራል፤ በርኵሰትም ጫፍ ላይ አጥፊው ይመጣል፤ እስከ ተቈረጠውም ፍጻሜ ድረስ መቅሠፍት በአጥፊው ላይ ይፈስሳል።