ኦሪት ዘዳግም 13:1-13
Ethiopian Amharic Bible (AMH)
1በመካከልህም ነቢይ ወይም ሕልም አላሚ ቢነሣ፥ ምልክትም ተአምራትም ቢሰጥህ፥
2እንደ ነገረህም ምልክቱ ተአምራቱም ቢፈጸም፥ እርሱም። ሄደን የማታውቃቸውን ሌሎች አማልክት እንከተል እናምልካቸውም ቢልህ፥
3አምላካችሁን እግዚአብሔርን በፍጹም ልባችሁ በፍጹምም ነፍሳችሁ ትወድዱት እንደ ሆነ ያውቅ ዘንድ አምላካችሁ እግዚአብሔር ሊፈትናችሁ ነውና የዚያን ነቢይ ቃል ወይም ያን ሕልም አላሚ አትስማ።
4አምላካችሁን አግዚአብሔርን ተከተሉ፥ እርሱንም ፍሩ፥ ትእዛዙንም ጠብቁ፥ ቃሉንም ስሙ፥ እርሱንም አምልኩ፥ ከእርሱም ጋር ተጣበቁ።
5አምላክህ እግዚአብሔር ትሄድባት ዘንድ ካዘዘህ መንገድ ሊያወጣህ፥ ከግብፅ ምድር ካወጣችሁ ከባርነትም ቤት ካዳናችሁ ከአምላካችሁ ከእግዚአብሔር ሊያስታችሁ ተናግሮአልና ያ ነቢይ ወይም ያ ሕልም አላሚ ይገደል፤ እንዲሁም ክፉውን ነገር ከመካከልህ አርቅ።
7የእናትህ ልጅ ወንድምህ ወይም ወንድ ልጅህ ወይም ሴት ልጅህ ወይም በብብትህ ያለች ሚስትህ ወይም እንደ ነፍስህ ያለ ወዳጅህ በስውር። ና፥ ሄደን ከምድር ዳር ጀምሮ እስከ ምድር ዳር ድረስ ወደ አንተ የቀረቡት ከአንተም የራቁት አንተን ከብበውህ ያሉ አሕዛብ ከሚያመልኩአቸው አማልክት፥ አንተም አባቶችህም የማታውቋቸውን ሌሎች አማልክት እናምልክ ብሎ ቢያስትህ፥ እሺ አትበለው፥
8አትስማውም፤ ዓይንህም አይራራለት፥ እትማረውም፥ አትሸሽገውም፤
9ነገር ግን ፈጽመህ ግደለው፤ እርሱን ለመግደል በፊት የአንተ እጅ፥ ከዚያም በኋላ የሕዝቡ ሁሉ እጅ በላዩ ትሁን።
10ከግብፅ ምድር ከባርነት ቤት ካወጣህ ከአምላክህ ከእግዚአብሔር ሊያርቅህ ወድዶአልና እስኪሞት ድረስ በድንጋይ ውገረው።
11እስራኤልም ሁሉ ሰምተው ይፈራሉ፥ እንዲህም ያለ ክፉ ሥራ እንደ ገና በአንተ መካከል አያደርጉም።
13ትፈልጋለህ፥ ትመረምራለህም፥ ትጠይቃለህም፤ እነሆም፥ እውነት ቢሆን፥ ይህም ክፉ ነገር በመካከልህ እንደ ተደረገ እርግጥ ሆኖ ቢገኝ፥
14የዚያችን ከተማ ሰዎች በሰይፍ ስለት ፈጽሞ ትመታቸዋለህ፤ ከተማይቱን፥ በእርስዋም ያለውን ሁሉ፥ እንስሳውንም በሰይፍ ስለት ታጠፋቸዋለህ።
15ዕቃዋንም ሁሉ ወደ አደባባይዋ ትሰበሰባለህ፥ ከተማይቱንም ዕቃዋንም ሁሉ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር በእሳት ፈጽመህ ታቃጥላለህ፤ ለዘላለምም ወና ትሆናለች፥ ደግሞም አትሠራም።