ኦሪት ዘዳግም 5:1-31
Ethiopian Amharic Bible (AMH)
1ሙሴም እስራኤልን ሁሉ ጠርቶ አላቸው። እስራኤል ሆይ፥ እንድትማሩአት በማድረግም እንድትጠብቁአት ዛሬ በጆሮአችሁ የምናገራትን ሥርዓትና ፍርድ ስሙ።
2አምላካችን እግዚአብሔር በኮሬብ ከእኛ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ።
3እግዚአብሔር ዛሬ በዚህ በሕይወት ካለነው ከእኛ ከሁላችን ጋር እንጂ ከአባቶቻችን ጋር ይህችን ቃል ኪዳን አላደረገም።
4በተራራው ላይ በእሳት ውስጥ ሆኖ እግዚአብሔር ፊት ለፊት ተናገራችሁ።
5እኔ የእግዚአብሔርን ቃል እነግራችሁ ዘንድ በዚያን ጊዜ በእግዚአብሔርና በእናንተ መካከል ቆሜ ነበር፤ እናንተ በእሳቱ ምክንያት ፈርታችኋልና፥ ወደ ተራራውም አልወጣችሁምና። እርሱም አለ።
6ከግብፅ ምድር ከባርነት ቤት ያወጣሁህ እግዚአብሔር አምላክህ እኔ ነኝ።
7ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይሁኑልህ።
8በላይ በሰማይ ካለው፥ በታችም በምድር ካለው፥ ከምድርም በታች በውኃ ካለው ነገር የማናቸውንም ምሳሌ የተቀረጸውንም ምስል ለአንተ አታድርግ፤
10የእግዚአብሔርን የአምላክህን ስም በከንቱ አትጥራ፤ እግዚአብሔር ስሙን በከንቱ የሚጠራውን ከበደል አያነጻውምና።
11እግዚአብሔር አምላክህ እንዳዘዘህ የሰንበትን ቀን ትቀድሰው ዘንድ ጠብቅ።
12ስድስት ቀን ሥራ ተግባርህንም ሁሉ አድርግ፥
13ሰባተኛው ቀን ግን ለእግዚአብሔር አምላክህ ሰንበት ነው፤ አንተ እንደምታርፍ ሎሌህና ገረድህ ያርፉ ዘንድ፥ አንተ ወንድ ልጅህም ሴት ልጅህም ሎሌህም ገረድህም በሬህም አህያህም ከብትህም ሁሉ በደጆችህም ውስጥ ያለ እንግዳ በእርሱ ምንም ሥራ አትሥሩ።
14አንተም በግብፅ ባሪያ እንደ ነበርህ አስብ፤ እግዚአብሔር አምላክህ በጸናች እጅና በተዘረጋ ክንድ ከዚያ አወጣህ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር አምላክህ የሰንበትን ቀን ትጠብቅ ዘንድ አዘዘህ።
15እግዚአብሔር አምላክህ እንዳዘዘህ አባትህንና እናትህን አክብር፤ እግዚአብሔር አምላክህ በሚሰጥህ ምድር ላይ ዕድሜህ እንዲረዝም፥ መልካምም እንዲሆንልህ።
16አትግደል።
17አታመንዝር።
18አትስረቅ።
19በባልንጀራህ ላይ በሐሰት አትመስክር።
20የባልጀራህን ሚስት አትመኝ፤ የባልንጀራህንም ቤት እርሻውንም ሎሌውንም ገረዱንም በሬውንም አህያውንም፥ ከባልንጀራህ ገንዘብ ሁሉ ማናቸውንም አትመኝ።
21እግዚአብሔር በተራራው ላይ በእሳትና በደመናው በጨለማውም ውስጥ ሆኖ በታላቅ ድምፅ እነዚህን ቃሎች ለጉባኤአችሁ ሁሉ ተናገረ፤ ምንም ምን አልጨመረም። በሁለቱም የድንጋይ ጽላቶች ላይ ጻፋቸው፥ ለእኔም ሰጣቸው።
22ተራራው በእሳት ሲነድድ ከጨለማው ውስጥ ድምፁን በሰማችሁ ጊዜ፥ እናንተ፥ የነገዶቻችሁ አለቆች ሽማግሌዎቻችሁም፥ ወደ እኔ ቀረባችሁ፤
23አላችሁም። እነሆ፥ አምላካችን እግዚአብሔር ክብሩንና ታላቅነቱን አሳይቶናል፥ ከእሳቱም ውስጥ ድምፁን ሰምተናል፤ እግዚአብሔርም ከሰው ጋር ሲነጋገር ሰውዮውም በሕይወት ሲኖር ዛሬ አይተናል።
24አሁን እንግዲህ ይህች ታላቂቱ እሳት ታቃጥለናለችና ለምን እንሞታለን? እኛ የአምላካችንን የእግዚአብሔርን ድምፅ ደግሞ ብንሰማ እንሞታለን።
25ከሥጋ ለባሽ ሁሉ እኛ እንደ ሰማን በእሳት ውስጥ ሆኖ ሲናገር የሕያው አምላክን ድምፅ ሰምቶ በሕይወቱ የኖረ ማን ነው?
26አንተ ቅረብ፥ አምላካችን እግዚአብሔር የሚለውን ሁሉ ስማ፤ አምላካችን እግዚአብሔርም ለአንተ የሚናገረውን ሁሉ ለእኛ ንገረን፤ እኛም ሰምተን እናደርገዋለን።
27በተናገራችሁኝም ጊዜ እግዚአብሔር የእናንተን ቃል ጽምፅ ሰማ፤ እግዚአብሔርም አለኝ። ይህ ሕዝብ የተናገሩህን ቃል ድምፅ ሰምቼአለሁ፤ የተናገሩህ ሁሉ መልካም ነገር ነው።
28ለእነርሱም ለዘላለምም ለልጆቻቸው መልካም ይሆንላቸው ዘንድ፥ እንዲፈሩኝ ሁልጊዜም ትእዛዜን ሁሉ እንዲጠብቁ እንዲህ ያለ ልብ ምነው በሆነላቸው!
29ሄደህ። ወደ ድንኳናችሁ ተመለሱ በላቸው።
30አንተ ግን በዚህ በእኔ ዘንድ ቁም፥ ርስት አድርጌ በምሰጣቸውም ምድር ላይ ያደርጉአት ዘንድ የምታስተምራቸውን ትእዛዜንና ሥርዓቴን ፍርዴንም ሁሉ እነግርሃለሁ።
31እግዚአብሔር አምላካችሁ እንዳዘዛችሁ ታደርጉ ዘንድ ጠብቁ፤ ከእርሱም ወደ ቀኝም ወደ ግራም ፈቀቅ አትበሉ።
32በሕይወት እንድትኖሩ፥ መልካምም እንዲሆንላችሁ፥ በምትወርሱአትም ምድር ዕድሜአችሁ እንዲረዝም፥ እግዚአብሔር አምላካችሁ ባዘዛችሁ መንገድ ሁሉ ሂዱ።