ኦሪት ዘጸአት 14:1-29
Ethiopian Amharic Bible (AMH)
1እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
2ተመልሰው በሚግዶልና በባሕር መካከል፥ በበኣልዛፎንም ፊት ለፊት ባለው በፊሀሒሮት ፊት እንዲሰፍሩ ለእስራኤል ልጆች ተናገር፤ ከእርሱም አጠገብ በባሕር ዳር ትሰፍራላችሁ።
3ፈርዖንም ስለ እስራኤል ልጆች። በምድር ይቅበዘበዛሉ፥ ምድረ በዳም ዘጋቻቸው ይላል።
4እኔም የፈርዖንን ልብ አጸናለሁ፥ እርሱም ያባርራቸዋል፤ በፈርዖንና በሠራዊቱም ሁሉ ላይ ክብር አገኛለሁ፤ ግብፃውያንም እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። እነርሱም እንዲሁ አደረጉ።
5ሕዝቡም እንደ ኰበለሉ ለግብፅ ንጉሥ ነገሩት፤ የፈርዖንና የባሪያዎቹም ልብ በሕዝቡ ላይ ተለወጠና። እንዳይገዛልን እስራኤልን የለቀቅነው ምን አድርገናል? አሉ።
6ሰረገላውንም አሰናዳ፥ ሕዝቡንም ከእርሱ ጋር ወሰደ፤
7ስድስት መቶ የተመረጡ ሰረገሎችንም፥ የግብፅንም ፈረሶች ሁሉ፥ በእያንዳንዱም ሰረገላ ሁሉ ላይ ሦስተኞችን ወሰደ።
8እግዚአብሔርም የግብፅን ንጉሥ የፈርዖንን ልብ አጸና፥ እርሱም የእስራኤልን ልጆች አሳደደ፤ የእስራኤልም ልጆች ከፍ ባለች እጅ ወጡ።
9ግብፃውያንም የፈርዖን ፈረሶች ሰረገሎቹም ፈረሰኞቹም ሠራዊቱም ሁሉ፥ አሳደዱአቸው፤ በባሕሩ ዳር በበኣልዛፎን ፊት ለፊት ባለው በፊሀሒሮት አጠገብ ሰፍረው አገኙአቸው።
10ፈርዖንም በቀረበ ጊዜ የእስራኤል ልጆች ዓይናቸውን አነሡ፥ እነሆም ግብፃውያን በኋላቸው ገሥግስው ነበር፤ የእስራኤልም ልጆች እጅግ ፈሩ፥ ወደ እግዚአብሔርም ጮኹ።
11ሙሴንም። በግብፅ መቃብር ስላልኖረ በምድረ በዳ እንሞት ዘንድ አወጣኸንን? ከግብፅ ታወጣን ዘንድ ይህ ያደረግህብን ምንድር ነው?
12በምድረ በዳ ከምንሞት ብንገዛላቸው ይሻላልና። ተወን፥ ለግብፃውያን እንገዛ ብለን በግብፅ ሳለን ያልንህ ቃል ይህ አይደለምን? አሉት።
13ሙሴም ለሕዝቡ። አትፍሩ፥ ዛሬ የምታዩአቸውን ግብፃውያንን ለዘላለም አታዩአቸውምና ቁሙ፥ ዛሬ ለእናንተ የሚያደርጋትን የእግዚአብሔርን ማዳን እዩ።
14እግዚአብሔር ስለ እናንተ ይዋጋል፥ እናንተም ዝም ትላላችሁ አላቸው።
15እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። ለምን ትጮኽብኛለህ? እንዲጓዙ ለእስራኤል ልጆች ንገር።
16አንተም በትርህን አንሣ፥ እጅህንም በባሕሩ ላይ ዘርጋ፥ ክፈለውም፤ የእስራኤልም ልጆች በባሕሩ ውስጥ በየብስ ያልፋሉ።
17እነሆም እኔ የግብፃውያንን ልብ አጸናለሁ፥ በኋላቸውም ይገባሉ፤ በፈርዖንና በሠራዊቱም ሁሉ በሰረገሎቹም በፈረሰኞቹም ላይ ክብር አገኛለሁ።
18ግብፃውያንም በፈርዖንና በሰረገሎቹ በፈረሰኞቹም ላይ ክብር ባገኘሁ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።
19በእስራኤልም ሠራዊት ፊት ይሄድ የነበረው የእግዚአብሔር መልአክ ፈቀቅ ብሎ በኋላቸው ሄደ፤ የደመናውም ዓምድ ከፊታቸው ፈቀቅ ብሎ በኋላቸው ቆመ፥
20በግብፃውያን ሰፈርና በእስራኤል ሰፈር መካከልም ገባ፤ በዚያም ደመናና ጨለማ ነበረ፥ በዚህ በኩል ግን ሌሊቱን አበራ፤ ሌሊቱንም ሁሉ እርስ በእርሳቸው አልተቃረቡም።
21ሙሴም በባሕሩ ላይ እጁን ዘረጋ፤ እግዚአብሔርም ሌሊቱን ሁሉ ጽኑ የምሥራቅ ነፋስ አምጥቶ ባሕሩን አስወገደው፥ ባሕሩንም አደረቀው፥ ውኃውም ተከፈለ።
22የእስራኤልም ልጆች በባሕሩ መካከል በየብስ ገቡ፤ ውኃውም በቀኛቸውና በግራቸው እንደ ግድግዳ ሆነላቸው።
23ግብፃውያንም፥ የፈርዖን ፈረሶችና ሰረገሎች ፈረሰኞቹም ሁሉ፥ እያሳደዱ በኋላቸው ወደ ባሕር መካከል ገቡ።
25እግዚአብሔርም ሙሴን። እጅህን በባሕሩ ላይ ዘርጋ፥ ውኃውም በግብፃውያን በሰረገሎቻቸውም በፈረሰኞቻቸውም ላይ ይመለስ አለው።
26ሙሴም እጁን በባሕሩ ላይ ዘረጋ፥ ባሕሩም ማለዳ ወደ መፍሰሱ ተመለሰ፤ ግብፃውያንም ከእርሱ ሸሹ፥ እግዚአብሔርም ግብፃውያንን በባሕሩ መካከል ጣላቸው።
27ውኃውም ተመልሶ በኋላቸው ወደ ባሕር የገቡትን ሰረገሎችን ፈረሰኞችንም የፈርዖንንም ሠራዊት ሁሉ ከደነ፤ ከእነርሱም አንድ ስንኳ አልቀረም።
28የእስራኤል ልጆች ግን በባሕሩ ውስጥ በየብስ ሄዱ፤ ውኆችም በቀኛቸውና በግራቸው እንደ ግድግዳ ሆኑላችው።
29እግዚአብሔር በዚያን ቀን እስራኤልን እንደዚህ ከግብፃውያን እጅ አዳነ፤ እስራኤልም የግብፃውያንን ሬሳ በባሕር ዳር አዩ።
30እስራኤልም እግዚአብሔር በግብፃውያን ላይ ያደረጋትን ታላቂቱን እጅ አዩ፥ ሕዝቡም እግዚአብሔርን ፈሩ፥ በእግዚአብሔርም በባሪያውም በሙሴ አመኑ።