መጽሐፈ ኢዮብ። 11:1-18
Ethiopian Amharic Bible (AMH)
1ነዕማታዊውም ሶፋር መለስ እንዲህም አለ።
2በውኑ ለቃል ብዛት መልስ መስጠት አይገባምን? ወይስ ተናጋሪ ሰው እንደ ጻድቅ ይቈጠራልን?
3ትምክህትህስ ሰዎችን ዝም ያሰኛቸዋልን? ብትሳለቅስ የሚያሳፍርህ የለምን?
4አንተ። ትምህርቴ የተጣራ ነው፥ በዓይንህም ፊት ንጹሕ ነኝ ትላለህ።
5ምነው እግዚአብሔር ቢናገርህ! በአንተም ላይ ከንፈሩን ቢከፍት!
6የጥበቡን ምሥጢር ቢገልጥልህ! ማስተዋሉ ብዙ ነውና። እግዚአብሔር ለበደልህ ከሚገባው አሳንሶ እንደሚያስከፍልህ እወቅ።
7የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር ልትመረምር ትችላለህን? ወይስ ሁሉን የሚችል አምላክ ፈጽመህ ልትመረምር ትችላለህን?
8ከሰማይ ይልቅ ከፍ ይላል፤ ምን ልታደርግ ትችላለህ? ከሲኦልም ይልቅ ይጠልቃል፤ ምን ልታውቅ ትችላለህ?
9ርዝመቱ ከምድር ይልቅ ይረዝማል፥ ከባሕርም ይልቅ ይሰፋል።
10እርሱ ቢያልፍ፥ ቢዘጋም፥ ጉባኤንም ቢሰበስብ፥ የሚከለክለው ማን ነው?
11ምናምንቴዎችን ሰዎች ያውቃልና፥ በደልንም ሲያይ ዝም ብሎ አይመለከትም።
12የሜዳ አህያ ግልገል ሰው ሆኖ ቢወለድ፥ ያን ጊዜ ከንቱ ሰው ጥበብን ያገኛል።
14በዚያን ጊዜ በእውነት ፊትህን ያለ ነውር ታነሣለህ፤ ትበረታለህ፥ አትፈራምም።
15መከራህንም ትረሳለህ፤ እንዳለፈ ውኃ ታስበዋለህ።
16ከቅትር ይልቅ ሕይወትህ ይበራል፤ ጨለማም ቢሆን እንደ ጥዋት ይሆናል።
17ተስፋም ስላለህ ተዘልለህ ትቀመጣለህ፤ በዙሪያህ ትመለከታለህ፥ በደኅንነትም ታርፋለህ።
18ትተኛለህ፥ የሚያስፈራህም የለም፤ ብዙ ሰዎችም ልመና ያቀርቡልሃል።
19የክፉዎች ዓይን ግን ትጨልማለች፤ የሚሸሹበትንም ያጣሉ፥ ተስፋቸውም ነፍሳቸውን ማውጣት ነው።