ኦሪት ዘሌዋውያን 11:1-45
Ethiopian Amharic Bible (AMH)
1እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው።
2ለእስራኤል ልጆች እንዲህ በሉአቸው። ከምድር እንስሶች ሁሉ የምትበሉአቸው እነዚህ ናቸው።
3የተሰነጠቀ ሰኮና ያለውንና የሚያመሰኳውን እንስሳ ሁሉ ብሉ።
4ነገር ግን ከሚያመሰኩት፥ ሰኮናቸው ስንጥቅ ከሆነው ከእነዚህ አትበሉም፤ ግመል ያመሰኳል፥ ነገር ግን ሰኮናው ስላልተሰነጠቀ በእናንተ ዘንድ ርኩስ ነው።
5ሽኮኮ ያመሰኳል፥ ነገር ግን ሰኰናው ስላልተሰነጠቀ በእናንተ ዘንድ ርኩስ ነው።
6ጥንቸልም ያመሰኳል፥ ነገር ግን ሰኮናው ስላልተሰነጠቀ በእናንተ ዘንድ ርኩስ ነው።
7እርያም ሰኮናው ተሰንጥቋል፥ ነገር ግን ስለማያመሰኳ በእናንተ ዘንድ ርኩስ ነው።
8የእነዚህን ሥጋ አትበሉም፥ በድናቸውንም አትነኩም፤ በእናንተ ዘንድ ርኩሶች ናቸው።
9በውኃ ውስጥ ከሚኖሩት ሁሉ እነዚህን ትበላላችሁ በውኆች በባሕሮችም በወንዞችም ውስጥ ከሚኖሩት ሁሉ ክንፍና ቅርፊት ያላቸውን ትበላላችሁ።
10በውኆቹ ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ፥ በውኆች ውስጥ የሕይወት ነፍስ ካላቸው ሁሉ፥ በባሕሮችና በወንዞች ውስጥ ክንፍና ቅርፊት የሌላቸው ሁሉ በእናንተ ዘንድ የተጸየፉ ናቸው።
11በእናንተም ዘንድ የተጸየፉ ይሆናሉ፤ ሥጋቸውንም አትበሉም፥ በድናቸውንም ትጸየፋላችሁ።
12ክንፍና ቅርፊትም የሌላቸው በውኃ ውስጥ የሚኖሩት ሁሉ በእናንተ ዘንድ የተጸየፉ ናቸው።
13ከወፎችም ወገን የምትጸየፉአቸው እነዚህ ናቸው፤ አይበሉም፤ የተጸየፉ ናቸው፤
14ንስር፥ ገዲ፥ ዓሣ አውጭ፥ ጭላት፥ ጭልፊት በየወገኑ፥
15ቁራ ሁሉ በየወገኑ፥
16ሰጎን፥ ጠላቋ፥ ዝዪ፥ በቋል በየወገኑ፥
18ይብራ፥ ጥምብ አንሣ አሞራ፥ ሽመላ፥ ሳቢሳ በየወገኑ፥ ጅንጁላቴ ወፍ፥ የሌሊት ወፍ።
19የሚበርርም፥ በአራት እግሮችም የሚሔድ ተንቀሳቃሽ ሁሉ በእናንተ ዘንድ የተጸየፈ ነው።
20ነገር ግን ከሚበርሩት፥ አራትም እግሮች ካሉአቸው፥ ከእግሮቻቸውም በላይ በምድር ላይ የሚዘልሉባቸው ጭኖች ካሉአቸው ተንቀሳቃሾች እነዚህን ትበላላችሁ።
21ከእነርሱም እነዚህን ትበላላችሁ፤ አራቱን ዓይነት አንበጣዎች በየወገናቸው።
22ነገር ግን የሚበርር፥ አራትም እግሮች ያሉት ተንቀሳቃሽ ሁሉ በእናንተ ዘንድ የተጸየፈ ነው።
23በእነዚህም ርኩስ ትሆናላችሁ፤ የእነርሱንም በድን የሚነካ ሁሉ እስከ ማታ ርኩስ ነው።
24ከእነርሱም በድን የሚያነሣ ሁሉ ልብሱን ይጠብ፥ እስከ ማታም ርኩስ ነው።
25ሰኮናም ያለው፥ ነገር ግን ሰኮናው ያልተሰነጠቀ፥ የማያመሰኳም እንሰሳ ሁሉ በእናንተ ዘንድ ርኩስ ነው፤ እርሱን የሚነካ ሁሉ ርኩስ ነው።
26በአራት እግሮቹ ከሚሄድ እንስሳ ሁሉ በመዳፎቹ ላይ የሚሄድ በእናንተ ዘንድ ርኩስ ነው፤ የእርሱን በድን የሚነካ ሁሉ እስከ ማታ ርኩስ ነው።
27በድናቸውንም የሚያነሣ ልብሱን ይጠብ፥ እስከ ማታም ርኩስ ነው። እነርሱም በእናንተ ዘንድ ርኩሶች ናቸው።
28በምድር ላይም ከሚንቀሳቀስ ተንቀሳቅሳሽ እነዚህ በእናንተ ዘንድ ርኩሶች ናቸው፤ ሙጭልጭላ፥ አይጥ፥ እንሽላሊት በየወገኑ፥
29ኤሊ፥ አዞ፥ ገበሎ፥ አርጃኖ፥ እስስት።
30ከሚንቀሳቀሱት ሁሉ በእናንተ ዘንድ ርኩሶች የሚሆኑ እነዚህ ናቸው። ከእነርሱም የሞተውን የሚነካ ሁሉ እስከ ማታ ርኩስ ነው።
31ከእነርሱም የሞተውን የሚነካ በምንም ላይ ቢወድቅ እርሱ ርኩስ ነው፤ የእንጨት ዕቃ ወይም ልብስ ወይም ቁርበት ወይም ከረጢት ቢሆን የሚሠራበት ዕቃ ሁሉ እርሱ በውኃ ውስጥ ይደረግ፥ እስከ ማታም ርኩስ ነው፤ ከዚያም በኋላ ንጹሕ ይሆናል።
32ከእነርሱም አንዳች በውስጡ የወደቀበትን የሸክላውን ዕቃ ሁሉ ስበሩት፥ በውስጡም ያለው ሁሉ ርኩስ ነው።
33በእርሱ ውስጥ ያለው፥ ውኃም የሚፈስስበት የሚበላ መብል ሁሉ ርኩስ ነው፤ በዚህም ዕቃ ሁሉ ያለው የሚጠጣ መጠጥ ሁሉ ርኩስ ነው።
34ከእነዚህም በድን የሚወድቅበት ሁሉ ርኩስ ነው፤ እቶን ወይም ምድጃ ቢሆን ይሰባበራል፤ ርኩሶች ናቸው፤ በእናንተ ዘንድ ርኩሶች ይሆናሉ።
35ነገር ግን ምንጩ፥ ጕድጓዱም፥ የውኃውም ኵሬ ንጹሐን ናቸው፤ በድናቸውን ግን የሚነካ ርኩስ ነው።
36ከበድናቸውም በሚዘራ ዘር ላይ አንዳች ቢወድቅ እርሱ ንጹሕ ነው።
37ነገር ግን በዘሩ ላይ ውኃ ቢፈስስበት፥ ከዚህ በኋላ ከበድናቸው አንዳች ቢወድቅበት፥ በእናንተ ዘንድ ርኩስ ነው።
38ለመብል ከሚሆኑላችሁ እንስሶች የሞተ ቢኖር፥ በድኑን የሚነካ ሁሉ እስከ ማታ ርኩስ ነው።
39ከበድኑም የሚበላ ልብሱን ያጥባል፥ እስከ ማታም ርኩስ ይሆናል፤ በድኑንም የሚያነሣ ልብሱን ይጠብ፥ እስከ ማታም ርኩስ ነው።
40በምድርም ላይ የሚንቀሳቀስ ተንቀሳቃሽ ሁሉ የተጸየፈ ነው፥ አትብሉትም።
41በሆዱ የሚሳብ፥ በአራትም እግሮች የሚሳብ፥ ብዙ እግሮችም ያሉት፥ በምድርም ላይ የሚንቀሳቀሱ ተንቀሳቃሾች ሁሉ የተጸየፉ ናቸውና አትብሉአቸው።
42በሚንቀሳቀሱ ተንቀሳቃሾች ሁሉ ሰውነታችሁን አታስጸይፉ፤ በእነርሱም እንዳትረክሱ ሰውነታችሁን አታርክሱባቸው።
43እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝና፤ ሰውነታችሁን ቀድሱ፥ ቅዱሳንም ሁኑ፥ እኔ ቅዱስ ነኝና፤ በምድርም ላይ በሚሳብ ተንቀሳቃሽ ሁሉ ሰውነታችሁን አታርክሱ።
44እኔ አምላካችሁ እሆን ዘንድ ከግብፅ ምድር ያወጣኋችሁ እግዚአብሔር ነኝ፤ እንግዲህ እኔ ቅዱስ ነኝና እናንተ ቅዱሳን ሁኑ።
45የእንስሳና የወፍ፥ በውኃም ውስጥ የሚንቀሳቀስ የፍጥረት ሁሉ፥ በምድርም ላይ የሚንቀሳቀስ የፍጥረት ሁሉ ሕግ ይህ ነው።
46በርኩስና በንጹሕ መካከል፥ የሕይወት ነፍስ ካላቸውም በምትበሉትና በማትበሉት መካከል እንድትለዩ ነው።