ኦሪት ዘሌዋውያን 22:1-31

Ethiopian Amharic Bible (AMH)

1እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።

2የእስራኤል ልጆች ለእኔ ከሚቀድሱአቸው ከቅዱሳን ነገሮች ራሳቸውን እንዲለዩ፥ የተቀደሰውንም ስሜን እንዳያረክሱ ለአሮንና ለልጆቹ ንገራቸው፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።

3እንዲህ በላቸው። ማናቸውም ሰው ከዘራችሁ በትውልዳችሁ ርኵሰት እያለበት የእስራኤል ልጆች ለእግዚአብሔር ወደሚቀድሱት ወደ ቅዱስ ነገር ቢቀርብ፥ ያ ሰው ከፊቴ ተለይቶ ይጥፋ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።

4ከአሮን ዘር ለምጽ ወይም ፈሳሽ ነገር ያለበት ሁሉ ንጹሕ እስኪሆን ድረስ ከተቀደሰው አይብላ። ከበድንም የተነሣ ርኩስ የሆነውን፥ ወይም ዘሩ ከእርሱ የሚፈስስበትን የሚነካ፥

5ወይም የሚያረክሰውን ተንቀሳቃሽ፥ ወይም በሁሉ ዓይነት የረከሰውን ሰው የሚነካ፥

6እነዚህን ሁሉ የሚነካ ሰው እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል፤ ገላውን በውኃ ካልታጠበ ከተቀደሰው አይብላ።

7ፀሐይም በገባች ጊዜ ንጹሕ ይሆናል፤ ከዚያም በኋላ እንጀራው ነውና ከተቀደሰው ይብላ።

8በእርሱም እንዳይረክስ፥ የሞተውን አውሬም የሰበረውን አይብላ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።

9ቢያረክሱአት እንዳይሞቱ ስለ እርስዋም ኃጢአትን እንዳይሸከሙ፥ ሕግን ይጠብቁ፤ የምቀድሳቸው እኔ እግዚአብሔር ነኝ።

10ልዩ ሰው ከተቀደሰው አይብላ የካህኑም እንግዳ ደመወዘኛውም ከተቀደሰው አይብላ።

11ካህኑ ግን በገንዘቡ ባሪያ ቢገዛ እርሱ ይብላው፤ በቤቱም የተወለዱት ከእንጀራው ይብሉ።

12የካህንም ልጅ ከልዩ ሰው ጋር ብትጋባ፥ እርስዋ ከተቀደሰው ቍርባን አትብላ።

13የካህን ልጅ ግን ባልዋ ቢሞት፥ ወይም ብትፋታ፥ ልጅም ባይኖራት፥ በብላቴንነትዋ እንደ ነበረች ወደ አባትዋ ቤት ብትመለስ፥ ከአባትዋ እንጀራ ትብላ፤ ልዩ ሰው ግን ከእርሱ አይብላ።

14ማናቸውም ሰው ሳያውቅ ከተቀደሰው ቢበላ አምስተኛ እጅ ጨምሮ የተቀደሰውን ለካህኑ ይስጥ።

16እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።

17ለአሮንና ለልጆቹ ለእስራኤልም ልጆች ሁሉ እንዲህ ብለህ ንገራቸው። ከእስራኤል ቤት ወይም ከእናንተ መካከል ከሚቀመጡት እንግዶች ማናቸውም ሰው ስእለቱን ሁሉ፥ በፈቃዱም የሚያቀርበውን ሁሉ፥ ለእግዚአብሔር ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚያቀርበውን ቍርባን ቢያቀርብ፥

18ይሠምርላችሁ ዘንድ ከበሬ ወይም ከበግ ወይም ከፍየል ነውር የሌለበትን ተባቱን አቅርቡ።

19ነገር ግን አይሠምርላችሁምና ነውር ያለበትን አታቅርቡ።

20ማናቸውም ሰው ስእለቱን ለመፈጸም ወይም በፈቃዱ ለማቅረብ የደኅንነትን መሥዋዕት፥ ወይም በሬን ወይም በግን፥ ለእግዚአብሔር ቢያቀርብ፥ ይሠምርለት ዘንድ ፍጹም ይሁን፥ ነውርም አይሁንበት።

21ዕውር ወይም ሰባራ ወይም ጕንድሽ ወይም የሚመግል ቍስል ያለበት ወይም እከካም ወይም ቋቍቻም ቢሆን፥ እነዚህን ሁሉ ለእግዚአብሔር አታቅርቡ፤ እነዚህም ለእሳት ቍርባን በመሠዊያው ላይ ለእግዚአብሔር አታሳርጉ።

22በሬው ወይም በጉ የተጨመረበት ወይም የጐደለበት ነገር ቢሆን፥ ለፈቃድ መሥዋዕት ማቅረብ ትችላለህ፤ ለስእለት ግን አይሠምርም።

23የተሰነጋውን ወይም የተቀጠቀጠውን ወይም የተሰበረውን ወይም የተቈረጠውን ለእግዚአብሔር አታቅርቡ፤ በምድራችሁም እነዚህን አትሠዉ።

24ከእነዚህም ከእንግዳ ሰው እጅ ለአምላካችሁ እንጀራ አታቅርቡ፤ ርኵሰትም ነውርም አለባቸውና አይሠምሩላችሁም።

25እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።

26በሬ ወይም በግ ወይም ፍየል ሲወለድ ሰባት ቀን ከእናቱ ጋር ይቀመጥ፤ በስምንተኛውም ቀን ከዚያም በላይ ለእግዚአብሔር የእሳት ቍርባን የሠመረ ይሆናል።

27ላም ወይም በግ ብትሆን እርስዋንና ልጅዋን በአንድ ቀን አትረዱ።

28የምስጋናንም መሥዋዕት ለእግዚአብሔር ስትሠዉ እንዲሠምርላችሁ ሠዉለት።

29በዚያው ቀን ይበላል፤ ከእርሱ እስከ ነገ ምንም አትተዉ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።

30ትእዛዛቴን ጠብቁ፥ አድርጉትም፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።

31የተቀደሰውንም ስሜን አታርክሱ፤ እኔ ግን በእስራኤል ልጆች መካከል እቀደሳለሁ፤

32የምቀድሳችሁ፥ አምላካችሁም እሆን ዘንድ ከግብፅ ምድር ያወጣኋችሁ እግዚአብሔር ነኝ። እኔ እግዚአብሔር ነኝ።