የሉቃስ ወንጌል 9:1-60

Ethiopian Amharic Bible (AMH)

1አሥራ ሁለቱንም ሐዋርያት በአንድነት ወደ እርሱ ጠርቶ በአጋንንት ሁሉ ላይ ደዌንም ይፈውሱ ዘንድ ኃይልና ሥልጣን ሰጣቸው፤

2የእግዚአብሔርንም መንግሥት እንዲሰብኩና ድውዮችን እንዲፈውሱ ላካቸው፥

3እንዲህም አላቸው። በትርም ቢሆን፥ ከረጢትም ቢሆን፥ እንጀራም ቢሆን፥ ብርም ቢሆን ለመንገድ ምንም አትያዙ፥ ሁለት እጀ ጠባብም አይሁንላችሁ።

4በማናቸውም በምትገቡበት ቤት በዚያ ተቀመጡ ከዚያም ውጡ።

5ማናቸውም የማይቀበሉአችሁ ቢሆኑ፥ ከዚያ ከተማ ወጥታችሁ ምስክር እንዲሆንባቸው ከእግራችሁ ትቢያ አራግፉ።

6ወጥተውም ወንጌልን እየሰበኩና በስፍራው ሁሉ እየፈወሱ በየመንደሩ ያልፉ ነበር።

7የአራተኛው ክፍል ገዥ ሄሮድስም የተደረገውን ነገር ሁሉ ሰምቶ፥ አንዳንድ ሰዎች።

8ዮሐንስ ከሙታን ተነሣ፥ ሌሎችም። ኤልያስ ተገለጠ፥ ሌሎችም። ከቀደሙት ነቢያት አንዱ ተነሥቶአል ይሉ ስለ ነበሩ አመነታ።

9ሄሮድስም። ዮሐንስንስ እኔ ራሱን አስቈረጥሁት፤ ይህ እንዲህ ያለ ነገር የምሰማበት ማን ነው? አለ። ሊያየውም ይሻ ነበር።

10ሐዋርያትም ተመልሰው ያደረጉትን ሁሉ ነገሩት። ከእርሱ ጋርም ወስዶአቸው ቤተ ሳይዳ ከምትባል ከተማ አጠገብ ወደ ምድረ በዳ ለብቻው ፈቀቅ አለ።

11ሕዝቡም አውቀው ተከተሉት፤ ተቀብሎአቸውም ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ይነግራቸው ነበር፥ መፈወስ ያስፈለጋቸውንም ፈወሳቸው።

12ቀኑም ይመሽ ጀመር፤ አሥራ ሁለቱም ቀርበው። በዚህ በምድረ በዳ ነንና በዙሪያችን ወዳሉ መንደሮችና ገጠሮች ሄደው እንዲያድሩና ምግብ እንዲያገኙ ሕዝቡን አሰናብት አሉት።

13እርሱ ግን። እናንተ የሚበሉትን ስጡአቸው አላቸው። እነርሱም። ሄደን ለዚህ ሁሉ ሕዝብ ምግብ ካልገዛን፥ ከአምስት እንጀራና ከሁለት ዓሣ የሚበልጥ የለንም አሉት፤

14አምስት ሺህ ሰዎች ያህሉ ነበርና። ለደቀ መዛሙርቱ። በየክፍሉ አምሳ አምሳውን አስቀምጡአቸው አላቸው።

15እንዲህም አደረጉ ሁሉንም አስቀመጡአቸው።

16አምስቱንም እንጀራና ሁለቱን ዓሣ ይዞ፥ ወደ ሰማይ አሻቅቦ አየና ባረካቸው ቆርሶም ለሕዝቡ እንዲያቀርቡ ለደቀ መዛርሙርቱ ሰጠ።

17ሁሉም በልተው ጠገቡ፥ ከእነርሱም የተረፈውን ቍርስራሽ አሥራ ሁለት መሶብ ወሰዱ።

18ለብቻውም ሲጸልይ ደቀ መዛሙርቱ ከእርሱ ጋር ነበሩና። ሕዝቡ እኔ ማን እንደ ሆንሁ ይላሉ? ብሎ ጠየቃቸው።

19እነርሱም መልሰው። መጥምቁ ዮሐንስ፥ ሌሎችም። ኤልያስ፥ ሌሎችም። ከቀደሙት ነቢያት አንዱ ተነሥቶአል ይላሉ አሉት።

20እናንተስ እኔ ማን እንደ ሆንሁ ትላላችሁ? አላቸው። ጴጥሮስም መልሶ። ከእግዚአብሔር የተቀባህ ነህ አለ።

22ለሁሉም እንዲህ አላቸው። በኋላዬ ሊመጣ የሚወድ ቢኖር፥ ራሱን ይካድ መስቀሉንም ዕለት ዕለት ተሸክሞ ይከተለኝ።

23ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታልና፤ ስለ እኔ ነፍሱን የሚያጠፋ ሁሉ ግን እርሱ ያድናታል።

24ሰው ዓለሙን ሁሉ አትርፎ ራሱን ቢያጠፋ ወይም ቢያጐድል ምን ይጠቅመዋል?

25በእኔና በቃሌ የሚያፍር ሁሉ፥ የሰው ልጅ በክብሩ በአባቱና በቅዱሳን መላእክቱ ክብርም ሲመጣ በእርሱ ያፍርበታል።

26እውነት እላችኋለሁ፥ በዚህ ከሚቆሙት ሰዎች የእግዚአብሔርን መንግሥት እስኪያዩ ድረስ ሞትን የማይቀምሱ አንዳንድ አሉ።

27ከዚህም ቃል በኋላ ስምንት ቀን ያህል ቈይቶ ጴጥሮስንና ዮሐንስን ያዕቆብንም ይዞ ሊጸልይ ወደ ተራራ ወጣ።

28ሲጸልይም የፊቱ መልክ ተለወጠ፤ ልብሱም ተብለጭልጮ ነጭ ሆነ።

29እነሆም፥ ሁለት ሰዎች እነርሱም ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር ይነጋገሩ ነበር፤

30በክብርም ታይተው በኢየሩሳሌም ሊፈጽም ስላለው ስለ መውጣቱ ይናገሩ ነበር።

31ነገር ግን ጴጥሮስንና ከእርሱ ጋር የነበሩት እንቅልፍ ከበደባቸው፤ ነቅተው ግን ክብሩንና ከእርሱ ጋር ቆመው የነበሩትን ሁለት ሰዎች አዩ።

32ከእርሱም ሲለዩ ጴጥሮስ ኢየሱስን። አቤቱ፥ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነውና አንድ ለአንተ አንድም ለሙሴ አንድም ለኤልያስ ሦስት ዳሶች እንሥራ አለው፤ የሚለውንም አያውቅም ነበር።

33ይህንም ሲናገር ደመና መጣና ጋረዳቸው፤ ወደ ደመናውም ሲገቡ ሳሉ ፈሩ።

34ከደመናውም። የመረጥሁት ልጄ ይህ ነው፥ እርሱን ስሙት የሚል ድምፅ መጣ።

35ድምፁም ከመጣ በኋላ ኢየሱስ ብቻውን ሆኖ ተገኘ። እነርሱም ዝም አሉ ካዩትም ነገር በዚያ ወራት ምንም ለማንም አላወሩም።

36በነገውም ከተራራ ሲወርዱ ብዙ ሕዝብ ተገናኙት።

37እነሆም፥ ከሕዝቡ አንድ ሰው እንዲህ እያለ ጮኸ። መምህር ሆይ፥ ለእኔ አንድ ልጅ ነውና ልጄን እንድታይልኝ እለምንሃለሁ።

38እነሆም፥ ጋኔን ይይዘዋል፥ ድንገትም ይጮኻል አረፋም እያስደፈቀው ያንፈራግጠዋል፥ እየቀጠቀጠም በጭንቅ ይለቀዋል፤

39ደቀ መዛሙርትህንም እንዲያወጡት ለመንሁ፥ አልቻሉምም።

40ኢየሱስም መልሶ። እናንተ የማታምን ጠማማ ትውልድ፥ እስከ መቼ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ? እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ? ልጅህን ወደዚህ አምጣው አለ።

41ሲቀርብም ጋኔኑ ጣለውና አንፈራገጠው፤ ኢየሱስ ግን ርኵሱን መንፈስ ገሥጾ ብላቴናውን ፈወሰው ለአባቱም መለሰው።

42ሁሉም ከእግዚአብሔር ታላቅነት የተነሣ ተገረሙ። ሁሉም ኢየሱስ ባደረገው ሁሉ ሲደነቁ፥

43ለደቀ መዛሙርቱ። የሰው ልጅ በሰው እጅ ይሰጥ ዘንድ አለውና እናንተ ይህን ቃል በጆሮአችሁ አኑሩ አለ።

44እነርሱ ግን ይህን ነገር አላስተዋሉም፥ እንዳይገባቸውም ተሰውሮባቸው ነበር፤ ስለዚህ ነገርም እንዳይጠይቁት ፈሩ።

45ከእነርሱም ማን እንዲበልጥ ክርክር ተነሣባቸው።

46ኢየሱስም የልባቸውን አሳብ አውቆ ሕፃንን ያዘ፤ በአጠገቡም አቁሞ።

47ማንም ይህን ሕፃን በስሜ የሚቀበል እኔን ይቀበላል፤ የሚቀበለኝም ሁሉ የላከኝን ይቀበላል፤ ከሁላችሁ የሚያንስ እርሱ ታላቅ ነውና አላቸው።

48ዮሐንስም መልሶ። አቤቱ፥ አንድ ሰው በስምህ አጋንንትን ሲያወጣ አየነው፥ ከእኛ ጋርም ስለማይከተል ከለከልነው አለው።

49ኢየሱስ ግን። የማይቃወማችሁ ከእናንተ ጋር ነውና አትከልክሉት አለው።

50የሚወጣበትም ወራት በቀረበ ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ ፊቱን አቀና፥

51በፊቱም መልክተኞችን ሰደደ። ሄደውም ሊያሰናዱለት ወደ አንድ ወደ ሳምራውያን መንደር ገቡ፤

52ፊቱም ወደ ኢየሩሳሌም እንደሚሄድ ስለ ነበረ አልተቀበሉትም።

53ደቀ መዛሙርቱም ያዕቆብና ዮሐንስ አይተው። ጌታ ሆይ፥ ኤልያስ ደግሞ እንዳደረገ እሳት ከሰማይ ወርዶ ያጥፋቸው እንል ዘንድ ትወዳለህን? አሉት።

54እርሱ ግን ዘወር ብሎ ገሠጻቸውና። ምን ዓይነት መንፈስ እንደ ሆነላችሁ አታውቁም፤

55የሰው ልጅ የሰውን ነፍስ ሊያድን እንጂ ሊያጠፋ አልመጣም አለ። ወደ ሌላ መንደርም ሄዱ።

56እነርሱም በመንገድ ሲሄዱ አንድ ሰው። ጌታ ሆይ፥ ወደ ምትሄድበት ሁሉ እከተልሃለሁ አለው።

57ኢየሱስም። ለቀበሮዎች ጕድጓድ ለሰማይም ወፎች መሳፈሪያ አላቸው፥ ለሰው ልጅ ግን ራሱን የሚያስጠጋበት የለውም አለው።

58ሌላውንም። ተከተለኝ አለው። እርሱ ግን። ጌታ ሆይ፥ አስቀድሜ ልሂድና አባቴን እቀብር ዘንድ ፍቀድልኝ አለ።

59ኢየሱስም። ሙታናቸውን እንዲቀብሩ ሙታንን ተዋቸው፤ አንተስ ሄደህ የእግዚአብሔርን መንግሥት ስበክ አለው።

60ደግሞ ሌላው። ጌታ ሆይ፥ እከተልሃለሁ፤ ነገር ግን አስቀድሜ ከቤቴ ሰዎች እንድሰናበት ፍቀድልኝ አለ።

61ኢየሱስ ግን። ማንም ዕርፍ በእጁ ይዞ ወደ ኋላ የሚመለከት ለእግዚአብሔር መንግሥት የተገባ አይደለም አለው።