መዝሙረ ዳዊት 78:1-68

Ethiopian Amharic Bible (AMH)

1ሕዝቤ ሆይ፥ ሕጌን አድምጡ፤ ጆሮአችሁንም ወደ አፌ ቃል አዘንብሉ።

2አፌን በምሳሌ እከፍታለሁ፤ ከቀድሞ ጀምሮ፥ ያለውንም ተምሳሊት እናገራለሁ።

3የሰማነውንና ያውቅነውን፥ አባቶቻችንም የነገሩንን፥ ለሚመጣ ትውልድ ከልጆቻቸው አልሰወሩም።

4የእግዚአብሔርን ምስጋናና ኃይሉን ያደረገውንም ተኣምራት ተናገሩ።

5ለልጆቻቸው ያስታውቅ ዘንድ ለአባቶቻችን ያዘዘውን ምስክር በያዕቆብ አቆመ፥ በእስራኤልም ሕግን ሠራ፤

6የሚመጣ፥ ትውልድ የሚወለዱም ልጆች ያውቁ ዘንድ፥ ተነሥተው ለልጆቻቸው ይነግራሉ፤

7ተስፋቸውን በእግዚአብሔር እንዲያደርጉ፥ የእግዚአብሔርንም ሥራ እንዳይረሱ፥ ትእዛዙንም እንዲጠብቁ፤

8እንደ አባቶቻቸው እንዳይሆኑ ጠማማና የምታስመርር ትውልድ፥ ልብዋን ያላቀናች ትውልድ፥ ነፍስዋ በእግዚአብሔር ዘንድ ያልታመነች።

9የኤፍሬም ልጆች ለሰልፍ ታጥቀው ቀስትንም ገትረው በሰልፍ ቀን ወደ ኋላ ተመለሱ።

10የእግዚአብሔርን ኪዳን አልጠበቁም፥ በሕጉም ለመመላለስ እንቢ አሉ፤

11መልካም ሥራውንና ያሳያቸውን ተኣምራቱን ረሱ፥

12በግብጽ አገርና በጣኔዎስ በረሃ በአባቶቻቸው ፊት የሠራውን ተኣምራት።

13ባሕርን ከፍሎ አሳለፋቸው፤ ውኆችን እንደ ክምር አቆመ።

14ቀን በደመና መራቸው፥ ሌሊቱንም ሁሉ በእሳት ብርሃን።

15ዓለቱን በምድረ በዳ ሰነጠቀ፤ ከጥልቅ እንደሚገኝ ያህል በብዙ አጠጣቸው።

16ውኃን ከጭንጫ አወጣ፥ ውኃንም እንደ ወንዞች አፈሰሰ።

17ነገር ግን ይበድሉት ዘንድ እንደ ገና ደገሙ፥ ልዑልንም በምድረ በዳ አስቈጡት።

18ለነፍሳቸው መብልን ይፈልጉ ዘንድ፥ እግዚአብሔርን በልባቸው ፈተኑት።

19እግዚአብሔርን እንዲህ ብለው አሙት። እግዚአብሔር በምድረ በዳ ማዕድን ያሰናዳ ዘንድ ይችላልን?

20ዓለቱን መታ፤ ውኆችም ወጡ፥ ወንዞችም ጐረፉ፤ እንጀራን መስጠትስ ይችላልን? ለሕዝቡስ ማዕድን ያዘጋጃልን?

21እግዚአብሔርም ይህን ሰምቶ ተቈጣ፤ በያዕቆብም ላይ እሳት ነደደ፥ መዓትም በእስራኤል ላይ መጣ፤

22በእግዚአብሔር አላመኑምና፥ በመድኃኒቱም አልተማመኑምና።

23ደመናውንም ከላይ አዘዘ፥ የሰማይንም ደጆች ከፈተ፤

24ይበሉም ዘንድ መናን አዘነበላቸው፥ የሰማይንም እንጀራ ሰጣቸው።

25የመላክትንም እንጀራ ሰው በላ ስንቅንም እስኪተርፋቸው ላከላቸው።

26ከሰማይ የምሥራቅን ነፋስ አስነሣ፥ በኃይሉም የደቡብን ነፋስ አመጣ፤

27ሥጋን እንደ አፈር፥ የሚበርሩትንም ወፎች እንደ ባሕር አሸዋ አዘነበላቸው፤

28በሰፈራቸው መካከል፥ በድንኳናቸውም ዙሪያ ወደቀ።

29በሉ እጅግም ጠገቡ፤ ምኞታቸውንም ሰጣቸው።

30ከወደዱትም አላሳጣቸውም፤ መብላቸውም ገና በአፋቸው ሳለ፥

31የእግዚአብሔር ቍጣ በላያቸው መጣ፥ ከእነርሱም ከፍ ያሉትን ገደለ፥ የእስራኤልንም ምርጦች አሰናከለ።

32ከዚህም ሁሉ ጋር እንደ ገና በደሉ፥ ተኣምራቱንም አላመኑም፤

33ቀኖቻቸውም በከንቱ አለቁ፥ ዓመቶቻቸውም በችኰላ።

34በገደላቸውም ጊዜ ወዲያው ፈለጉት፤ ተመለሱ ወደ እግዚአብሔርም ገሠገሡ፤

35ረዳታቸውም እግዚአብሔር፥ መድኃኒታቸውም ልዑል አምላክ እንደ ሆነ አሰቡ።

37እርሱ ግን መሓሪ ነው፥ ኃጢአታቸውንም ይቅር አላቸው፥ አላጠፋቸውምም፤ ቍጣውንም መመለስ አበዛ፥ መዓቱንም ሁሉ አላቃጠለም።

38ወጥቶ የማይመለስ መንፈስ፥ ሥጋም እንደ ሆኑ አሰበ።

39በምድረ በዳ ምን ያህል አስቈጡት፥ በበረሃም አሳዘኑት።

40ተመለሱ፥ እግዚአብሔርንም ፈተኑት፥ የእስራኤልንም ቅዱስ አሳዘኑት።

41እነርሱም እጁን አላሰቡም፥ ከጠላቶቻቸው እጅ ያዳነበትን ቀን፥

42በግብጽ ያደረገውን ተኣምራቱን፥ በጣኔዎስም በረሃ ያደረገውን ድንቁን።

43ወንዞቻቸውንም ወደ ደም ለወጠ፥ ምንጮቻቸውን ደግሞ እንዳይጠጡ።

44ዝንቦችንም በላያቸው ሰደደባቸው፥ በሉአቸውም፤ በጓጉንቸርም አጠፋቸው።

45ፍሬያቸውን ለኩብኩባ፥ ሥራቸውንም ለአንበጣ ሰጠ።

46ወይናቸውን በበረዶ፥ በለሳቸውንም በአመዳይ አጠፋ።

47እንስሶቻቸውን ለበረዶ፥ ሀብታቸውንም ለእሳት ሰጠ።

48የመዓቱን መቅሠፍት በላያቸው ሰደደ፤ መቅሠፍትን መዓትንም መከራንም በክፉዎች መላእክት ሰደደ።

49ለቍጣው መንገድን ጠረገ፤ ነፍሳቸውንም ከሞት አላዳናትም፥ እንስሶቻቸውንም በሞት ውስጥ ዘጋ፤

50በኵሮቻቸውን ሁሉ በግብጽ፥ የድካማቸውንም መጀመሪያ በካም ድንኳኖች ገደለ።

51ሕዝቡን ግን እንደ በጎች አሰማራቸው፥ እንደ መንጋም በምድረ በዳ መራቸው።

52በተስፋም መራቸው አልፈሩምም፥ ጠላቶቻቸውንም ባሕር ደፈናቸው።

53ወደ መቅደሱም ተራራ አገባቸው፥ ቀኙ ወደ ፈጠረችው ወደዚህች ተራራ፤

54ከፊታቸውም አሕዛብን አባረረ፥ ርስቱንም በገመድ አካፈላቸው፥ የእስራኤልንም ወገኖች በቤታቸው አኖረ።

55ነገር ግን ልዑል እግዚአብሔርን ፈተኑት አስቈጡትም፥ ምስክሩንም አልጠበቁም፤

56ተመለሱም እንደ አባቶቻቸውም ከዱ፤ እንደ ጠማማ ቀስትም ተገለበጡ፤

57በኰረብታ መስገጃዎቻቸውም አስቈጡት፥ በተቀረጹ ምስሎቻቸውም አስቀኑት።

58እግዚአብሔርም ይህን ሰምቶ ተቈጣ፥ እስራኤልንም እጅግ ናቀ፤

59የሴሎምን ማደሪያ ተዋት በሰዎች መካከል ያደረገባትን ድንኳኑን፤

60ኃይላቸውን ለምርኮ፥ ሽልማቱንም በጠላት እጅ ሰጠ።

61ሕዝቡንም በጦር ውስጥ ዘጋቸው፥ ርስቱንም ቸል አላቸው።

62ጕልማሶቻቸውን እሳት በላቸው፥ ቈነጃጅቶቻቸውም አላዘኑም፤

63ካህናቶቻቸውም በሰይፍ ወደቁ፥ ባልቴቶቻቸውም አላለቀሱላቸውም።

64እግዚአብሔርም ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ተነሣ፥ የወይን ስካር እንደ ተወው እንደ ኃያልም ሰው፤

65ጠላቶቹንም በኋላቸው መታ፤ የዘላለምን ኀሣር ሰጣቸው።

66የዮሴፍንም ድንኳን ተዋት፥ የኤፍሬምንም ወገን አልመረጠውም፤

67የይሁዳን ወገን ግን መረጠ፥ የወደደውን የጽዮንን ተራራ።

68መቅደሱን እንደ አርያም ሠራ፥ ለዘላለምም በምድር ውስጥ መሠረታት።

69ዳዊትንም ባሪያውን መረጠው፥ ከበጎቹም መንጋ ውስጥ ወሰደው፤