መዝሙረ ዳዊት 94:1-21
Ethiopian Amharic Bible (AMH)
1እግዚአብሔር የበቀል አምላክ ነው። የበቀል አምላክ ተገለጠ።
2የምድር ፈራጅ ሆይ፥ ከፍ ከፍ በል፤ ለትዕቢተኞች ፍዳቸውን ክፈላቸው።
3አቤቱ፥ ኃጢአተኞች እስከ መቼ? ኃጢአተኞች እስከ መቼ ይጓደዳሉ?
4ይከራከራሉ፥ ዓመፃንም ይናገራሉ፤ ዓመፃንም የሚያደርጉ ሁሉ ይናገራሉ።
5አቤቱ፥ ሕዝብን አዋረዱ፥ ርስትህንም አስቸገሩ።
6ባልቴቲቱንና ድሀ አደጉን ገደሉ፥ ስደተኛውንም ገደሉ።
7እግዚአብሔር አያይም፥ የያዕቆብ አምላክ አያስተውልም አሉ።
8የሕዝብ ደንቆሮች ሆይ፥ አስተውሉ፤ ሰነፎችማ መቼ ይጠበባሉ?
9ጆሮን የተከለው አይሰማምን? ዓይንን የሠራው አያይምን?
10አሕዛብንስ የሚገሥጸው፥ ለሰውም እውቀት የሚያስተምረው እርሱ አይዘልፍምን?
11የሰዎች አሳብ ከንቱ እንደ ሆነ እግዚአብሔር ያውቃል።
13እግዚአብሔር ሕዝቡን አይጥልምና፥ ርስቱንም አይተውምና
14ፍርድ ወደ ጽድቅ እስኪመልስ ድረስ ልበ ቅኖችም ሁሉ ይከተሉአታል።
15በክፉዎች ላይ ለእኔ የሚቆም ማን ነው? ዓመፃንስ በሚያደርጉ ላይ ለእኔ የሚከራከር ማን ነው?
16እግዚአብሔር የረዳኝ ባይሆን ነፍሴ ለጥቂት ጊዜ በሲኦል ባደረች ነበር።
17እግሮቼ ተሰናከሉ ባልሁ ጊዜ፥ አቤቱ፥ ምሕረትህ ረዳኝ።
18አቤቱ፥ ለልቤ እንደ መከራዋ ብዛት ማጽናናትህ ነፍሴን ደስ አሰኛት።
19በሕግ ላይ ዓመፅን የሚሠራ የዓመፅ ዙፋን ከአንተ ጋር አንድ ይሆናልን?
20የጻድቅን ነፍስ ያደቡባታል፥ በንጹሕ ደምም ይፈርዳሉ።
21እግዚአብሔር መጠጊያ ሆነኝ፥ አምላኬ የተስፋዬም ረዳት ነው።
22እንደ በደላቸውም እንደ ክፋታቸውም ፍዳቸውን ይከፍላቸዋል፥ አምላካችን እግዚአብሔርም ያጠፋቸዋል።