ኦሪት ዘዳግም 29:1-25
Ethiopian Amharic Bible (AMH)
1እግዚአብሔር በኮሬብ ካደረገው ቃል ኪዳን ሌላ በሞዓብ ምድር ከእስራኤል ልጆች ጋር ያደርገው ዘንድ ሙሴን ያዘዘው የቃል ኪዳኑ ቃሎች እነዚህ ናቸው።
2ሙሴም የእስራኤልን ልጆች ሁሉ ጠርቶ አላቸው። እግዚአብሔር በፊታችሁ በግብፅ ምድር በፈርዖንና በባሪያዎቹ ሁሉ በምድሩም ሁሉ ያደረገውን ሁሉ፥
3ዓይኖቻችሁ ያዩአቸውን ታላላቆች ፈተናዎች፥ ታላላቆች ተአምራትና ድንቆች፥ አይታችኋል፤
4እግዚአብሔር ግን አስተዋይ ልብ፥ የሚያዩ ዓይኖች፥ የሚሰሙም ጆሮች እስከ ዛሬ ድረስ አልሰጣችሁም።
5አርባ ዓመት በምድረ በዳ መራኋችሁ፤ ልብሳችሁም አላረጀባችሁም፥ ጫማችሁም በእግራችሁ ላይ አላረጀም።
6እኔ አምላካችሁ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቁ ዘንድ እንጀራ አልበላችሁም፥ የወይን ጠጅና የሚያሰክረውን መጠጥ አልጠጣችሁም።
7ወደዚህም ስፍራ በመጣችሁ ጊዜ የሐሴቦን ንጉሥ ሴዎን የባሳንም ንጉስ ዐግ ሊወጉን ወጡብን፥ እኛም መታናቸው፤
8ምድራቸውንም ወስደን ለሮቤልና ለጋድ ለምናሴም ነገድ እኵሌታ ርስት አድርገን ሰጠናቸው።
9ስለዚህ በምታደርጉት ሁሉ ትከናወኑ ዘንድ የዚህን ቃል ኪዳን ቃሎች ጠብቁ አድርጉም።
12እኔም ይህን ቃል ኪዳንና ይህን መሐላ የማደርገው ከእናንተ ጋር ብቻ አይደለም፤
13ነገር ግን ዛሬ በአምላካችን በእግዚአብሔር ፊት ከእኛ ጋር በዚህ ከሚቆም ሰው ጋር፥ ዛሬም ከእኛ ጋር በዚህ ከሌለ ሰው ጋር ነው እንጂ፤
14ነገር ግን እኛ በግብፅ ምድር እንደ ተቀመጥን በመካከላቸውም ባለፋችሁባቸው አሕዛብ መካከል እንዳለፍን አውቃችኋልና፥
15ርኩስነታቸውንም በእነርሱም ዘንድ የነበሩትን የእንጨትና የድንጋይ የብርና የወርቅም ጣዖቶቻቸውን አይታችኋልና፥
16ሄዶ የእነዚያን አሕዛብ አማልክት ያመልክ ዘንድ ከአምላኩ ከእግዚአብሔር ልቡን ዛሬ የሚያስት ወንድ ወይም ሴት ወይም ወገን ወይም ነገድ አይኑርባችሁ፤ ሐሞትና እሬትም የሚያበቅል ሥር አይሁንባችሁ።
17የዚህንም እርግማን ቃሎች የሰማ ሰው። ምንም እንኳ በልቤ ደንዳንነት ብሄድ፥ ለጥማቴም ስካር ብጨምር፥ ሰላም ይሆንልኛል ብሎ ሰውነቱን በልቡ የሚባርክ ቢኖር፥
18የእግዚአብሔር ቍጣ ቅንዓቱም በዚያ ሰው ላይ ይጤሳል እንጂ እግዚአብሔር ይቅርታ አያደርግለትም፤ በዚህም መጽሐፍ የተጻፈው እርግማን ሁሉ በላዩ ይኖራል፥ እግዚአብሔርም ስሙን ከሰማይ በታች ይደመስሰዋል።
19እግዚአብሔርም በዚህ ሕግ መጽሐፍ እንደ ተጻፈው እንደ ቃል ኪዳኑ እርግማን ሁሉ ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ ለጥፋት ይለየዋል።
20ከዚያም በኋላ የሚነሣ ትውልድ ከእናንተም በኋላ የሚሆኑ ልጆቻችሁ ከሩቅ አገርም የሚመጣ እንግዳ፥ የዚህን አገር መቅሠፍት፥ እግዚአብሔርም በእርስዋ ያደረገውን ሥቃይዋን፥
21ምድርም በሁለንተናዋ ዲንና ጨው መቃጠልም እንደ ሆነባት፥ እንዳትዘራም እንዳታበቅልም፥ ማናቸውም ሣርና ልምላሜም እንዳይወጣባት፥ እግዚአብሔር በቍጣውና በመዓቱ እንደ ገለባበጣቸው እንደ ሰዶምና ገሞራ እንደ አዳማና እንደ ሲባዮ እንደ ሆነች ባዩ ጊዜ፥
22አሕዛብ ሁሉ። እግዚአብሔር በዚህች ምድር ስለ ምን እንደዚህ አደረገ? ይህስ የቍጣው ታላቅ መቅሠፍት ምንድር ነው? ይላሉ።
23ሰዎችም እንዲህ ይላሉ። የአባቶቻቸው አምላክ እግዚአብሔር ከግብፅ ምድር ባወጣቸው ጊዜ ከእነርሱ ጋር ያደረገውን ቃል ኪዳን ስለተዉ፥
24ሄደውም የማያውቋቸውንና ያልታዘዙትን ሌሎችን አማልክት ስላመለኩና ስለ ሰገዱላቸው፥
25ስለዚህ በዚህ መጽሐፍ የተጻፈውን መርገም ሁሉ ያወርድባት ዘንድ የእግዚአብሔር ቍጣ በዚህች ምድር ነደደ፤
26ዛሬም እንዳሉ እግዚአብሔር በቍጣና በመቅሠፍት በታላቅም መዓት ከምድራቸው ነቀላቸው፥ ወደ ሌላም ምድር ጣላቸው።
27ምሥጢሩ ለአምላካችን ለእግዚአብሔር ነው፤ የተገለጠው ግን የዚህን ሕግ ቃሎች ሁሉ እናደርግ ዘንድ ለእኛ ለዘላለምም ለልጆቻችን ነው።