ኦሪት ዘዳግም 30:1-18

Ethiopian Amharic Bible (AMH)

1እንዲህም ይሆናል፤ እኔ በፊትህ ያኖርሁት ይህ ነገር ሁሉ፥ በረከቱና መርገሙ፥ በወረደብህ ጊዜ፥ አምላክህም እግዚአብሔር በሚበትንህ በአሕዛብ ሁሉ መካከል ሆነህ በልብህ ባሰብኸው ጊዜ፥

2ወደ አምላክህም ወደ እግዚአብሔር ተመልሰህ እኔ ዛሬ እንደማዝዝህ ሁሉ አንተና ልጆችህ በፍጹም ልብና በፍጹም ነፍስ ለቃሉ በታዘዝህ ጊዜ፥

3አምላክህ እግዚአብሔር ምርኮህን ይመልሳል ይራራልህማል፤ አምላክህም እግዚአብሔር አንተን ከበተነበት ከአሕዛብ ሁሉ መካከል መልሶ ይሰበስብሃል።

4ሰዎችህም እስከ ሰማይ ዳርቻ ድረስ ፈልሰው እንደ ሆነ አምላክህ እግዚአብሔር ከዚያ ይሰበስብሃል፥ ከዚያም ያመጣሃል።

5አባቶችህም ወደ ወረሱአት ምድር አምላክህ እግዚአብሔር ያጋባሃል፥ ትወርሳትማለህ፤ መልካምም ያደርግልሃል፥ ከአባቶችህም ይልቅ ያበዛሃል።

6በሕይወትም እንድትኖር፥ አምላክህን እግዚአብሔርን በፍጹም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ እንድትወድድ አምላክህ እግዚአብሔር ልብህን የዘርህንም ልብ ይገርዛል።

7አምላክህም እግዚአብሔር ይህችን መርገም ሁሉ በጠላቶችህና በሚጠሉህ በሚያሳድዱህም ላይ ያመጣታል።

8አንተም ተመልሰህ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ቃል ትሰማለህ፥ ዛሬም እኔ የማዝዝህን ትእዛዙን ሁሉ ታደርጋለህ።

10እኔ ዛሬ የማዝዝህ ይህች ትእዛዝ ከባድ አይደለችም፥ ከአንተም የራቀች አይደለችም።

11ሰምተን እናደርጋት ዘንድ ስለ እኛ ወደ ሰማይ ወጥቶ እርስዋን የሚያመጣልን ማን ነው? እንዳትል በሰማይ አይደለችም።

12ሰምተን እናደርጋት ዘንድ ስለ እኛ ባሕሩን ተሻግሮ እርስዋን የሚያመጣልን ማን ነው? እንዳትል ከባሕሩ ማዶ አይደለችም።

13ነገር ግን ታደርገው ዘንድ ቃሉ በአፍህና በልብህ ውስጥ ለአንተ እጅግ ቅርብ ነው።

14ተመልከት፤ ዛሬ በፊትህ ሕይወትንና መልካምነትን፥ ሞትንና ክፋትን አኑሬአለሁ።

15በሕይወትም እንድትኖር እንድትባዛም፥ አምላክህም እግዚአብሔር ልትወርሳት በምትገባባት ምድር እንዲባርክህ፥ አምላክህን እግዚአብሔርን ትወድድ ዘንድ፥ በመንገዱም ትሄድ ዘንድ ትእዛዙንና ሥርዓቱን ፍርዱንም ትጠብቅ ዘንድ ዛሬ እኔ አዝዝሃለሁ።

16ልብህ ግን ቢስት አንተም ባትሰማ፥ ብትታለልም፥ ለሌሎችም አማልክት ብትሰግድ ብታመልካቸውም፥

17ፈጽማችሁ እንድትጠፉ እኔ ዛሬ እነግራችኋለሁ፤ ዮርዳኖስን ተሻግረህ ትወርሳት ዘንድ በምትገባባት ምድር ዘመናችሁን አታስረዝሙም።

18በፊታችሁ ሕይወትንና ሞትን በረከትንና መርገምን እንዳስቀመጥሁ እኔ ዛሬ ሰማይንና ምድርን በአንተ ላይ አስመሰክራለሁ፤ እንግዲህ አንተና ዘርህ በሕይወት ትኖሩ ዘንድ ሕይወትን ምረጥ፤

19እግዚአብሔርም ለአባቶችህ ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም እንዲሰጣቸው በማለላቸው በምድሪቱ ትቀመጥ ዘንድ፥ እርሱ ሕይወትህ የዘመንህም ርዝመት ነውና አምላክህን እግዚአብሔርን ትወድደው ትጠባበቀውም ቃሉንም ትሰማ ዘንድ ምረጥ።