ኦሪት ዘኍልቍ 31:1-52

Ethiopian Amharic Bible (AMH)

1እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።

2ስለ እስራኤል ልጆች በቀል ምድያማውያንን ተበቀል፤ ከዚያም በኋላ ወደ ወገኖችህ ትከማቻለህ።

3ሙሴም ሕዝቡን። ከእናንተ መካከል ሰዎች ለጦርነት ይሰለፉ፤ ስለ እግዚአብሔር በቀል ምድያምን ይበቀሉ ዘንድ በምድያም ላይ ይሂዱ፤

4ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ ከየነገዱ አንድ ሺህ ሰው ወደ ጦርነት ስደዱ ብሎ ተናገራቸው።

5ከእስራኤልም አእላፋት አሥራ ሁለት ሺህ፥ ከየነገዱ አንድ አንድ ሺህ፥ ለጦርነት የተሰለፉ ሰዎች ተሰጡ።

6ሙሴም ከየነገዱ አንድ አንድ ሺህ ወደ ጦርነት ሰደደ፤ እነርሱንና የካህኑን የአልዓዛርን ልጅ ፊንሐስን ወደ ጦርነት ሰደዳቸው፤ የመቅደሱንም ዕቃ የሚነፋውንም መለከት በእጁ ሰጠው።

7እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘ ከምድያም ጋር ተዋጉ፥ ወንዶችንም ሁሉ ገደሉ።

8ከተገደሉትም ጋር የምድያምን ነገሥታት ገደሉአቸው፤ አምስቱም የምድያም ነገሥታት ኤዊ፥ ሮቆም፥ ሱር፥ ሑር፥ ሪባ ነበሩ፤ የቢዖርንም ልጅ በለዓምን ደግሞ በሰይፍ ገደሉት።

9የእስራኤልም ልጆች የምድያምን ሴቶችና ልጆቻቸውን ማረኩ፤ እንስሶቻቸውንና መንጎቻቸውንም ዕቃቸውንም ሁሉ በዘበዙ።

10የተቀመጡባቸውን ከተሞቻቸውን ሁሉ ሰፈሮቻቸውንም ሁሉ በእሳት አቃጠሉ።

11የሰውንና የእንስሳን ምርኮና ብዝበዛ ሁሉ ወሰዱ።

12የማረኩአቸውንም ሰዎች ምርኮውንና ብዝበዛውን ወደ ሙሴና ወደ ካህኑ ወደ አልዓዛር ወደ እስራኤልም ልጆች ማኅበር፥ በዮርዳኖስም አጠገብ በኢያሪኮ ፊት ለፊት በሞዓብ ሜዳ ወዳለው ሰፈር አመጡ።

13ሙሴና ካህኑ አልዓዛርም የማኅበሩም አለቆች ሁሉ ከሰፈሩ ወደ ውጭ ሊገናኙአቸው ወጡ።

14ሙሴም ከዘመቻ በተመለሱት በጭፍራ አለቆች፥ በሻለቆችና በመቶ አለቆች ላይ ተቈጣ።

15ሙሴም አላቸው። በውኑ ሴቶችን ሁሉ አዳናችኋቸውን?

16እነሆ፥ እነዚህ በፌጎር ምክንያት በበለዓም ምክር እግዚአብሔርን ይበድሉ ዘንድ ለእስራኤል ልጆች ዕንቅፋት ሆኑ፤ ስለዚህም በእግዚአብሔር ማኅበር ላይ መቅሠፍት ሆነ።

17አሁን እንግዲህ ከልጆቹ ወንዱን ሁሉ ግደሉ፥ ወንድንም በመኝታ የሚያውቁትን ሴቶች ሁሉ ግደሉ።

18ወንድን የማያውቁትን ሴቶች ልጆችን ሁሉ ግን ለራሳችሁ አድኑአቸው።

19ከሰፈሩም ውጭ ሰባት ቀን ስፈሩ፤ ሰውን የገደለ ሁሉ የተገደለውንም የዳሰሰ ሁሉ፥ እናንተ የማረካችኋቸውም በሦስተኛውና በሰባተኛው ቀን ሰውነታችሁን ንጹሕ አድርጉ።

20ልብስንም፥ ከቁርበትም የተዘጋጀውን ሁሉ፥ ከፍየልም ጠጕር ከእንጨትም የተሠራውን ሁሉ ንጹሕ አድርጉ።

21ካህኑም አልዓዛር ከሰልፍ የመጡትን ሰዎች አላቸው። እግዚአብሔር ሙሴን ያዘዘው የሕጉ ሥርዓት ይህ ነው፤

22ወርቁንና ብሩን፥ ናሱንም፥ ብረቱንም፥ ቆርቆሮውንም፥

23አረሩንም፥ በእሳት ለማለፍ የሚችለውን ሁሉ በእሳት ታሳልፉታላችሁ፥ ንጹሕም ይሆናል፤ ነገር ግን በማንጻት ውኃ ደግሞ ይጠራል። በእሳትም ለማለፍ የማይችለውን በውኃ ታሳልፉታላችሁ።

24በሰባተኛውም ቀን ልብሳችሁን እጠቡ፥ ንጹሕም ትሆናላችሁ፤ ከዚያም በኋላ ወደ ሰፈሩ ትቀርባላችሁ።

25እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።

26አንተና ካህኑ አልዓዛር የማኅበሩም አባቶች አለቆች የተማረኩትን ሰውና እንስሳ ቍጠሩ።

27ምርኮውንም በተዋጉትና ወደ ሰፍል በወጡት፥ በማኅበሩም ሁሉ መካከል አስተካክለህ ክፈል።

28ከእነዚያም ከተዋጉት ወደ ሰልፍም ከወጡት ሰልፈኞች ዘንድ፥ ከሰዎችም ከበሬዎችም ከአህዮችም ከመንጎችም ከአምስት መቶ አንድ ለእግዚአብሔር ግብር አውጣ።

29ከድርሻቸው ወስደህ ለእግዚአብሔር ለማንሣት ቍርባን ለካህኑ ለአልዓዛር ስጠው።

30ከእስራኤልም ልጆች ድርሻ ከሰዎች ከበሬዎችም ከአህዮችም ከመንጎችም ከከብቶችም ሁሉ ከአምሳ አንድ ትወስዳለህ፥ የእግዚአብሔርንም ማደሪያ አገልግሎት ለሚጠብቁ ለሌዋውያን ትሰጣለህ።

31ሙሴና ካህኑ አልዓዛርም እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው አደረጉ።

32ወደ ሰልፍ የወጡ ሰዎችም ከወሰዱት ብዝበዛ ያስቀሩት ምርኮ እንዲህ ሆነ፤ ስድስት መቶ ሰባ አምስት ሺህ በጎች፥

34ወንድ ከማያውቁ ሴቶችም ሠላሳ ሁለት ሺህ ነፍስ።

35በዘመቻም ለነበሩ ሰዎች ድርሻ የሆነ እኵሌታ ከበግ ሦስት መቶ ሠላሳ ሰባት ሺህ አምስት መቶ በጎች ነበረ፥

36ከበጎችም የእግዚአብሔር ግብር ስድስት መቶ ሰባ አምስት ነበረ።

37በሬዎችም ሠላሳ ስድስት ሺህ አምስት መቶ ነበሩ፤ የእግዚአብሔርም ግብር ሰባ ሁለት ነበረ።

38አህዮቹም ሠላሳ ሺህ አምስት መቶ ነበሩ፤ የእግዚአብሔርም ግብር ስድሳ አንድ ነበረ።

39ሰዎቹም አሥራ ስድስት ሺህ ነበሩ፤ የእግዚአብሔርም ግብር ሠላሳ ሁለት ነበረ።

40እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው ሙሴ ለእግዚአብሔር ለማንሣት ቍርባን የሆነውን ግብር ለካህኑ ለአልዓዛር ሰጠው።

41ከእስራኤል ልጆች እኩሌታም፥ ወደ ሰልፍ ከወጡት ወንዶች ላይ ሙሴ የለየው፥

42የማኅበሩ ድርሻ ሦስት መቶ ሠላሳ ሰባት ሺህ አምስት መቶ በጎች፥

43ሠላሳ ስድስት ሺህ በሬዎች፥

44ሠላሳ ሺህ አምስት መቶ አህዮች፥

45አሥራ ስድስት ሺህ ሰዎች ነበሩ።

46ከእስራኤል ልጆች ድርሻ ሙሴ ከሰውና ከእንስሳ ከአምሳ አንድ ወሰደ፥ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው የእግዚአብሔርን ማደሪያ አገልግሎት ለሚጠብቁ ሌዋውያን ሰጠ።

47በሠራዊት አእላፋት ላይ የተሾሙት አለቆች፥ ሻለቆችና የመቶ አለቆች፥ ወደ ሙሴ ቀረቡ፥

48ሙሴንም። እኛ ባሪያዎችህ ወደ ሰልፍ የወጡትን ከእጃችን በታች ያሉትን ቈጠርን፥ ከእኛም አንድ አልጐደለም።

49ሰውም ሁሉ ካገኘው ከወርቅ ዕቃ፥ ከእግር አልቦም፥ ከአምባርም፥ ከቀለበትም፥ ከጕትቻም፥ ከድሪውም ለነፍሳችን በእግዚአብሔር ፊት ያስተሰርይልን ዘንድ ለእግዚአብሔር መባ አምጥተናል አሉት።

50ሙሴና ካህኑ አልዓዛርም ወርቁንና በልዩ ልዩ የተሠራውን ዕቃ ሁሉ ከእጃቸው ተቀበሉ።

51ሻለቆችም የመቶ አለቆችም ለእግዚአብሔር ለማንሣት ቍርባን ያቀረቡት ወርቅ ሁሉ አሥራ ስድስት ሺህ ሰባት መቶ አምሳ ሰቅል ነበረ።

52ወደ ሰልፍ የወጡ ሰዎች ሁሉ ከምርኮአቸው ለራሳቸው ወሰዱ።

53ሙሴና ካህኑ አልዓዛርም ወርቁን ከሻለቆችና ከመቶ አለቆች ወስደው በእግዚአብሔር ፊት ለእስራኤል ልጆች መታሰቢያ ወደ መገናኛው ድንኳን አገቡት።