ኦሪት ዘኍልቍ 32:1-39
Ethiopian Amharic Bible (AMH)
1የሮቤልና የጋድ ልጆችም እጅግ ብዙ እንስሶች ነበሩአቸው፤ እነሆም፥ የኢያዜር ምድርና የገለዓድ ምድር ለእንስሶች የተመቸ ስፍራ እንደ ነበረ ባዩ ጊዜ፥
2የጋድና የሮቤል ልጆች መጥተው ሙሴንና ካህኑን አልዓዛርን የማኅበሩንም አለቆች እንዲህ ብለው ተናገሩአቸው።
4እግዚአብሔር በእስራኤል ማኅበር ፊት የመታው ምድር፥ አጣሮት፥ ዲቦን፥ ኢያዜር፥ ነምራ፥ ሐሴቦን፥ ኤልያሊ፥ ሴባማ፥ ናባው፥ ባያን፥ ለእንስሶች የተመቸ ምድር ነው፤ ለእኛም ለባሪያዎችህ እንስሶች አሉን።
5እኛስ በአንተ ዘንድ ሞገስን አግኝተን እንደ ሆነ ይህን ምድር ለባሪያዎችህ ርስት አድርገህ ስጠን፤ ወደ ዮርዳኖስም ማዶ አታሻግረን።
6ሙሴም ለጋድና ለሮቤል ልጆች አላቸው። ወንድሞቻችሁ ወደ ጦርነት ሲሄዱ እናንተ በዚህ ትቀመጣላችሁን?
7እግዚአብሔር ወደሚሰጣቸው ምድር እንዳይሻገሩ የእስራኤልን ልጆች ልብ ለምን ታደክማላችሁ?
8ምድሪቱን ይሰልሉ ዘንድ ከቃዴስ በርኔ በሰደድኋቸው ጊዜ አባቶቻችሁ እንዲህ አደረጉ።
9ወደ ኤሽኮልም ሸለቆ በሄዱ ጊዜ፥ ምድሪቱንም ባዩ ጊዜ፥ እግዚአብሔር ወደ ሰጣቸው ምድር እንዳይገቡ የእስራኤልን ልጆች ልብ አደከሙ።
10በዚያም ቀን የእግዚአብሔር ቍጣ ነደደ፥
12የእግዚአብሔርም ቍጣ በእስራኤል ላይ ጸና፥ በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ያደረገ ትውልድ ሁሉ እስኪጠፋ ድረስ አርባ ዓመት በምድረ በዳ ውስጥ አቅበዘበዛቸው።
13እነሆም፥ የእግዚአብሔርን መዓት በእስራኤል ላይ አብዝታችሁ ትጨምሩ ዘንድ እናንተ የኃጢአተኞች ትውልድ በአባቶቻችሁ ፋንታ ቆማችኋል።
14እርሱን ከመከተል ብትመለሱ እርሱ ሕዝቡን በምድረ በዳ ደግሞ ይተዋል፤ ይህንንም ሕዝብ ሁሉ ታጠፋላችሁ።
15ወደ እርሱም ቀርበው አሉት። በዚህ ለእንስሶቻችን በረቶች ለልጆቻችንም ከተሞች እንሠራለን፤
16እኛ ግን ለጦርነት ተዘጋጅተን ወደ ስፍራቸው እስክናገባቸው ድረስ በእስራኤል ልጆች ፊት እንሄዳለን፤ በዚህም ምድር ስላሉ ሰዎች ልጆቻችን በተመሸጉ ከተሞች ይቀመጣሉ።
17የእስራኤል ልጆች ሁሉ ርስታቸውን እስኪወርሱ ድረስ ወደ ቤቶቻችን አንመለስም፤
18ከዮርዳኖስ ወዲህ ወደ ምሥራቅ ርስታችን ደርሶናልና እኛ ከዮርዳኖስ ማዶ ወደዚያ ከእነርሱ ጋር ርስት አንወርስም።
19ሙሴም አላቸው። ይህንስ ነገር ብታደርጉ፥ ተዘጋጅታችሁም በእግዚአብሔር ፊት ወደ ሰልፍ ብትሄዱ፥
20እርሱም ጠላቶቹን ከፊቱ እስኪያሳድድ ድረስ ምድሪቱም በእግዚአብሔር ፊት ድል እስክትሆን ድረስ ከእናንተ ሰው ሁሉ ጋሻ ጦሩን ይዞ በእግዚአብሔር ፊት ዮርዳኖስን ቢሻገር፥
21ከዚያ በኋላ ትመለሳላችሁ፥ በእግዚአብሔርም ፊት በእስራኤል ዘንድ ንጹሐን ትሆናላችሁ፤ ይህች ምድርም በእግዚአብሔር ፊት ርስት ትሆንላችኋለች።
22እናንተ ግን እንዲህ ባታደርጉ፥ እነሆ፥ እግዚአብሔርን ትበድላላችሁ፤ ኃጢአታችሁም እንዲያገኛችሁ እወቁ።
23ለልጆቻችሁ ከተሞች፥ ለበጎቻችሁም በረቶች ሥሩ፤ ከአፋችሁም የወጣውን ነገር አድርጉ።
24የጋድና የሮቤልም ልጆች ሙሴን እንዲህ ብለው ተናገሩት። እኛ ባሪያዎችህ ጌታችን እንዳዘዘ እናደርጋለን።
25ልጆቻችን፥ ሚስቶቻችንም፥ መንጎቻችንም፥ እንስሶቻችንም ሁሉ በዚያ በገለዓድ ከተሞች ይሆናሉ፤
26እኛ ባሪያዎችህ ግን ሁላችን ጋሻ ጦራችንን ይዘን በእግዚአብሔር ፊት ጌታችን እንደ ተናገረ ወደ ጦርነት እንሄዳለን።
27ሙሴም ካህኑን አልዓዛርን የነዌንም ልጅ ኢያሱን የእስራኤልንም ልጆች ነገድ አለቆች ስለ እነርሱ አዘዘ።
28ሙሴም። የጋድና የሮቤል ልጆች ሁላቸው ጋሻ ጦራቸውን ይዘው ከእናንተ ጋር በእግዚአብሔር ፊት ዮርዳኖስን ቢሻገሩ፥ ምድሪቱንም ድል ብትነሡ፥ የገለዓድን ምድር ርስት አድርጋችሁ ትሰጡአቸዋላችሁ።
29ጋሻ ጦራቸውን ይዘው ከእናንተ ጋር ባይሻገሩ ግን በከነዓን ምድር በእናንተ መካከል ርስታቸውን ይወርሳሉ አላቸው።
30የጋድና የሮቤልም ልጆች መልሰው። እግዚአብሔር ለእኛ ለባሪያዎችህ እንደ ተናገረ እንዲሁ እናደርጋለን።
31ጋሻ ጦራችንን ይዘን በእግዚአብሔር ፊት ወደ ከነዓን ምድር እንሻገራለን፥ ከዮርዳኖስም ማዶ ከወዲሁ የወረስነው ርስት ይሆንልናል አሉት።
32ሙሴም ለጋድና ለሮቤል ልጆች ለዮሴፍም ልጅ ለምናሴ ነገድ እኩሌታ፥ የአሞራውያንን ንጉሥ የሴዎንን ግዛት የባሳንንም ንጉሥ የዐግን ግዛት፥ ምድሪቱንና በዙሪያዋ ያሉትን ከተሞች ሰጣቸው።
33የጋድም ልጆች ዲቦንን፥ አጣሮትን፥ አሮዔርን፥
34ዓጥሮትሽፋንን፥ ኢያዜርን፥ ዮግብሃን፥
35ቤትነምራን፥ ቤትሃራንን የተመሸጉ ከተሞች አድርገው ሠሩ፤ የበጎች በረቶችንም ሠሩ።
36የሮቤልም ልጆች ሐሴቦንን፥ ኤልያሊን፥
37ቂርያታይምን፥ ስማቸውም የተለወጠውን ናባውን፥ በኣልሜዎንን፥ ሴባማን ሠሩ፤ እነዚህንም የሠሩአቸውን ከተሞች በሌላ ስም ጠሩአቸው።
38የምናሴም ልጅ የማኪር ልጆች ወደ ገለዓድ ሄዱ፥ ወሰዱአትም፥ በእርስዋም የነበሩትን አሞራውያንን አሳደዱ።
39ሙሴም ለምናሴ ልጅ ለማኪር ገለዓድን ሰጠ፤ በእርስዋም ተቀመጠ።
40የምናሴም ልጅ ኢያዕር ሄዶ መንደሮችዋን ወሰደ፥ የኢያዕርም መንደሮች ብሎ ጠራቸው።
41ኖባህም ሄደ ቄናትንም መንደሮችዋንም ወሰደ፥ በስሙም ኖባህ ብሎ ጠራቸው።