መዝሙረ ዳዊት 106:1-42
Ethiopian Amharic Bible (AMH)
1ሃሌ ሉያ፤ ቸር ነውና፥ ምህረቱም ለዘላለም ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ።
2የእግዚአብሔርን ኃይል ሥራ ማን ይናገራል? ምስጋናውንስ ሁሉ ማን ያሰማል?
3ፍርድን የሚጠብቁ፥ ጽድቅንም ሁልጊዜ የሚያደርጉ ምስጉኖች ናቸው።
4አቤቱ፥ በሕዝብህ ሞገስ አስበን፥ በመድኃኒትህም ጐብኘን፤
5የመረጥሃቸውን በጎነት እናይ ዘንድ፥ በሕዝብህም ደስታ ደስ ይለን ዘንድ፥ ከርስትህም ጋር እንጓደድ ዘንድ።
6ከአባቶቻችን ጋር ኃጢአትን ሠራን፥ ዐመፅንም፥ በደልንም።
7አባቶቻችን በግብጽ ሳሉ ተኣምራትህን አላስተዋሉም፥ የምሕረትህንም ብዛት አላሰቡም፤ በኤርትራ ባሕር ባለፉ ጊዜ ዐመፁብህ።
8ኃይሉን ግን ለማስታወቅ። ስለ ስሙ አዳናቸው።
9የኤርትራንም ባሕር ገሠጸ እርሱም ደረቀ፤ እንደ ምድረ በዳ በጥልቅ መራቸው።
10ከሚጠሉአቸውም እጅ አዳናቸው፥ ከጠላትም እጅ ተቤዣቸው።
11ያሳደዱአቸውንም ውኃ ደፈናቸው፥ ከእነርሱም አንድ አልቀረም።
12በዚያን ጊዜ በቃሉ አመኑ፥ ምስጋናውንም ዘመሩ።
13ፈጥነውም ሥራውን ረሱ፥ በምክሩም አልታገሡም።
14በምድረ በዳም ምኞትን ተመኙ፥ በበረሃም እግዚአብሔርን ተፈታተኑት።
15የለመኑትንም ሰጣቸው፤ ለነፍሳቸው ግን ክሳትን ላከ።
16ሙሴንም እግዚአብሔር የቀደሰውንም አሮንን በሰፈር ተመቀኙአቸው።
17ምድርም ተከፈተች ዳታንንም ዋጠችው፥ የአቤሮንንም ወገን ደፈነች፤
18በማኅበራቸውም እሳት ነደደች፥ ነበልባልም ኅጥኣንን አቃጠላቸው።
19በኮሬብም ጥጃን ሠሩ፥ ቀልጦ ለተሠራ ምስልም ሰገዱ።
20ሣርም በሚበላ በበሬ ምሳሌ ክብራቸውን ለወጡ።
22እንዳያጠፋቸው ቍጣውን ይመልስ ዘንድ የተመረጠው ሙሴ በመቅሠፍት ጊዜ በፊቱ ባይቆም ኖሮ፥ ያጠፋቸው ዘንድ ተናገረ።
23የተወደደችውን ምድር ናቁ፥ በቃሉም አልታመኑም፥
24በድንኳኖቻቸውም ውስጥ አንጐራጐሩ፤ የእግዚአብሔርን ቃል አልሰሙም።
26በብዔል ፌጎርም ተባበሩበት፥ የሙታንንም መሥዋዕት በሉ።
27በሥራቸውም አስመረሩት፥ ቸነፈርም በላያቸው በዛ።
28ፊንሐስም ተነሥቶ ፈረደባቸው፥ ቸነፈሩም ተወ፤
29ያም እስከ ዘላለም ለልጅ ልጅ ጽድቅ ሆኖ ተቈጠረለት።
31እግዚአብሔርም እንዳላቸው አሕዛብን አላጠፉም፤
32ከአሕዛብም ጋር ተደባለቁ፥ ሥራቸውንም ተማሩ።
33ለጣዖቶቻቸውም ተገዙ፥ ወጥመድም ሆኑባቸው።
34ወንዶች ልጆቻቸውንና ሴቶች ልጆቻቸውን ለአጋንንት ሠው፤
35የወንዶች ልጆቻቸውንና የሴቶች ልጆቻቸን ደም፥ ለከነዓን ጣዖቶች የሠውአቸውን ንጹሕ ደም አፈሰሱ፥ ምድርም በደም ረከሰች።
36በሥራቸው ረከሱ፥ በማድረጋቸውም አመነዘሩ።
37የእግዚአብሔርም ቍጣ በሕዝቡ ላይ ነደደ፥ ርስቱንም ተጸየፈ።
38ወደ አሕዛብም እጅ አሳለፋቸው፥ የሚጠሉአቸውም ገዙአቸው።
39ጠላቶቻቸውም ግፍ አደረጉባቸው፥ ከእጃቸውም በታች ተዋረዱ።
40ብዙ ጊዜ አዳናቸው፤ ነገር ግን በምክራቸው አስመረሩት፥ በኃጢአታቸውም ተዋረዱ።
41እርሱ ግን ጩኸታቸውን በሰማ ጊዜ ጭንቃቸውን ተመለከተ፤
42ለእነርሱም ኪዳኑን አሰበ፥ እንደ ምሕረቱም ብዛት ተጸጸተ።
43በማረኩአቸውም ሁሉ ፊት ሞገስን ሰጣቸው።
44አምላካችን እግዚአብሔር ሆይ፥ አድነን፤ ቅዱስ ስምህን እናመሰግን ዘንድ፥ በምስጋናህም እንመካ ዘንድ፥ ከአሕዛብ መካከል ሰብስበን።
45ከዘላለም እስከ ዘላለም የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይባረክ ሕዝብም ሁሉ አሜን ይበል። ሃሌ ሉያ።